ምክር ቤቱ 48 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት አጸደቀ

97

አዲስ  አበባ፤ ግንቦት 21/2012 (ኢዜአ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌዴራል መንግስት በኮሮናቫይረስ   ምክንያት እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለማለፍ ያቀረበውን ተጨማሪ የ48 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በጀት  አጸደቀ።

ምክር ቤቱ በሌሎች ጉዳዮች ላይም ውይይት አድርጓል።

5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ልዩ ስብሰባውን በዛሬው ዕለት አድርጓል።

ምክር ቤቱ በዛሬ ስብሰባው በአገሪቷ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እያስከተለ ያለውን ምጣኔ ኃብታዊ ጫና ለመቋቋም የሚያግዝ ተጨማሪ በጀት ነው ያጸደቀው።

ወረርሽኙ በጤና፣ በማሕበራዊና በምጣኔ ኃብት ላይ የሚያሳደረው ጫና ከፍተኛ በመሆኑ መንግስት የተለያዩ እርምጃዎች እየወሰደ መሆኑ ተገልጿል።

የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ችግሩ በአንድ በኩል የመንግስት ገቢ እንዲቀንስ ሲያደርግ በሌላ በኩል ደግሞ ወጪውን እንዲጨምር ማድረጉን ለምክር ቤቱ አብራርተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው ''ሁኔታው የአገሪቷ ዓመታዊ እድገት ከ2 እስከ 3 በመቶ ቀንሶ እድገቷ ከ5 እስከ 6 በመቶ እንደማይበልጥ ጥናቶች አመላክተዋል'' ብለዋል።

መንግስት እስካሁን ችግሩን ለመቋቋም በ2012 በጀት ዓመት ከተፈቀደው ውስጥ ከ12 እስከ 15 ቢሊዮን ብር ጥቅም ላይ እየዋለ ቢሆንም ይህ ብቻ በቂ ባለመሆኑ ተጨማሪ 48 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ማስፈለጉን ተናግረዋል።

ይህንን ወጪ ለመሸፈንም ከልማት አጋሮች በበጀት ድጋፍ መልክ 28 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር እርዳታና ብድር ተገኝቷል ነው ያሉት።

የተቀረው 20 ቢሊዮን ብር ደግሞ ከአገር ውስጥ ብድር ለመሸፈን መታቀዱንም ጨምረው ገልጸዋል።

በአገሪቷ እስካሁን በቋሚነት ሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር በኮቪድ-19 ምክንያት እንደሚጨምርም ተገልጿል።

ይህ ሁሉ ፍላጎት ባለበት አገሪቷ በበሽታው ምክንያት የታክስና ታክስ ያልሆኑ የገቢ አይነቶች እስከ 11 ቢሊዮን ልታጣ እንደምትችል ተጠቁሟል።

  የበጀቱን አጠቃቀም ለምክር ቤቱ  ማብራሪያ  የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ''ከተመደበው በጀት ውስጥ 38 ቢሊዮን ብር የሚሆነው ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ለተለዩ ዜጎች ሰብዓዊ እርዳታ ይውላል'' ብለዋል።

ከአገር ውስጥ በብድር መልኩ ለማግኘት ከታቀደው ውስጥ 10 ቢሊዮኑ ቀጥታ ከብሔራዊ ባንክ የሚገኝ ሲሆን የቀረው 10 ቢሊዮን ብር ደግሞ ከቦንድ ሽያጭ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ይህ መሆኑ ደግሞ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ላይ የዋጋ ግሽበት እንዳያስከትል እገዛ ያደርጋል ነው ያሉት።

''በጥቅሉ የጸደቀው በጀት የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ለማቅረብና ለሰብዓዊ እርዳታ የሚውል ነው'' ብለዋል።

ምክር ቤቱ ከተወያየባቸው አጀንዳዎች መካከል የ'ልዩ መንግስት ዕዳ ሰነድ' ሲሆን ይህም የልማት ባንክን የካፒታል አቅም ለመጨመር ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ የተመራው አንዱ ነው።

ይህም ባንኩ የተባለሹ ብድሮች ክምችትን ለመሰረዝ፣ የካፒታል በቂነት ምጣኔ አስተማማኝ ለማድረግና የባንኩን የተከፈለ ካፒታል ለማሳደግ የታሰበ ነው ተብሏል።

ባንኩ ባለው ወቅታዊ ካፒታል መጠንና በማቋቋሚያ ደንብ ረቂቅ ማሻሻያ ላይ የተመለከተውን ብር ልዩነት ወለድ በማይታሰብበት የመንግስት ዕዳ ሰነድ እንዲከፈል የሚጠይቅ አጭር መግለጫ ቀርቧል።

ይሁን እንጂ የተወሰኑ የምክር ቤት አባላት ''ቀድሞውኑ የከፋ ችግር ውስጥ ለሚገኘው ልማት ባንክ ይህንን ማድረጉ ተገቢ ባለመሆኑ ነገሩ በደንብ መታየት አለበት'' ብለዋል።

አንድ የምክር ቤቱ አባል መርጦ የወከላቸው ህዝብ ባለበት ወረዳ 22 የሚደርሱ ባለሃብቶች የእርሻ መሬት ተረክበው ከባንኩ እስከ 10 ሚሊዮን ብር ብድር ወስደው 10 ዓመት ሙሉ ምንም ሳይሰሩ ቆይቷል።

''እነዚህ የባንኩን ገንዘብ በቡድን የከፋፈሉ ግለሰቦች 'ሃመር ይነዳሉ፤ ዱባይ ይዝናናሉ' መሬቱም ጦሙን አድሯል፤ የህዝብ ገንዘብም ባክኗል'' ነው ያሉት።  

የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ባንኩን በተመለከተ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ የተመራለት የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጉዳዩን በትኩረት እንዲያየው አሳስበዋል።

በተመሳሳይ ምክር ቤቱ የኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽንን ለመደንገግ የቀረበ ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ያጸደቀ ሲሆን የጂኦተርማል ማሻሻያ አዋጅንም አጽድቋል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅና የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አማኞች አብያተ ክርስትያናት ሕብረት ካውንስል ህጋዊ ሰውነት ለመስጠት የተዘጋጀውንም ረቂቅ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም