በጌዴኦ ዞን በ26 ሚሊዮን ብር የተገነቡ የውሃና የመስኖ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት በቁ

81

ዲላ፣ ግንቦት 21/2012 (ኢዜአ)  በጌዴኦ ዞን ላለፉት ሁለት ዓመታት በግንባታ ላይ የነበሩ የልማት ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውን የዞኑ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት መምሪያ ገለጸ።
በዞኑ የተሰሩ የልማት ፕሮጀክቶች  በክልልና በዞን ከፍተኛ አመራሮች ዛሬ ተጎብኝተዋል።

የመምሪያው ተወካይ አቶ ዮሐንስ ታደሰ በሰጡት ማብራሪያ በወናጎና ገደብ ወረዳዎች በመንግስት በጀት የተገነቡ የመስኖና የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት በቅተዋል ።

"የመስኖ እርሻ ለዘላቂ ልማትና ንጹህ የመጠጥ ውሃ ለማህበረሰብ" በሚል መርህ የተካሔዱ ግንባታዎች ናቸው ብለዋል ።

በወናጎ ወረዳ በባንቲ-ሲቡና ሀሴ-ሀሮ ቀበሌዎች ሁለት ምንጮች የማጎልበት ስራ የተከናወነ ሲሆን በዚህም ከ50 ሺህ በላይ የአካባቢው ነዋሪዎች የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ  ሆነዋል።

በገደብ ወረዳ ጨልጨሌ ቀበሌ የተገነባው የመስኖ ፕሮጀክት ደግሞ አርሶ አደሩ ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ አመቱን ሙሉ የግብርና ስራውን እንዲያከናውን አጋዥ እንደሚሆን ጠቁመዋል።

የመስኖ አውታሩ ከ60 ሄክታር በላይ መሬት በማልማት ከ500 በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የማድረግ አቅም እንዳለው ጠቅሰዋል።

እስከ አሁን 240 አርሶ አደሮች በክላስተር ተደራጅተው ወደ ልማት ስራው መግባታቸውንም አቶ ዮሐንስ ገልጸዋል።

የገደብ ወረዳ አርሶ አደር ተስፋዬ ሻንቆ በሰጡት አስተያየት የመስኖ ልማት ተሳታፊ መሆናቸው ከዚህ ቀደም በዓመት አንድ ጊዜ ከሚያመርቱት የብርእ ሰብሎች በተጓዳኝ የተለያዩ የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ በማልማት የገቢ ምንጫቸውን ለማስፋት ያግዛቸዋል ።

የመስኖ ፕሮጀክቶቹ በአካባቢያቸው መገንባቱ ከባህላዊ መስኖ ልማት በማላቀቅ በዘመናዊ መንገድ በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ አጋዥ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ  ሌላው አርሶ አደር ከፍያለው ቦዶ ናቸው።

ምንም እንኳን የዘር አቅርቦት እጥረት ቢኖርም የኮሮና ቫይረስ መከሰት በግብርና ምርት ላይ የሚያደርሰውን ጫና ለመቀነስ በአጭር ጊዜ በሚደርሱ አትክልቶች ላይ በማተኮር እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

የደቡብ ክልል ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ  ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አሰፋ ታደሰ በጉብኝቱ ወቅት እንደተናገሩት የመስኖ ልማት ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና በአጭር ጊዜ በማረጋገጥ ተጠቃሚነቱን እንደሚያሳደግ ገልጸዋል።

በግብዓት አቅርቦት ረገድ ያለውን ማነቆ በመፍታት አርሶ አደሩን ውጤታማ ለማድረግ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

ወቅቱ ክረምት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የመስኖ ተፋሰሱ በደለል እንዳይሞላ አርሶ አደሩ ክትትል ማድረግ እንዳለበት  ምክትል የቢሮ ሃላፊው አሳስበዋል።

በወረርሽኙ ሳቢያ የምርት እጥረት እንዳይከሰትም ሁሉንም የውሃ አማራጮች አሟጦ ለመጠቀም በየደረጃው ርብርብ እንደሚደረግ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም