በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓት 137ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ተያዙ

116

አዲስ  አበባ  ግንቦት 21/2012 (ኢዜአ) በዛሬው ዕለት ብቻ ተጨማሪ 137 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ሲገኝባቸው የ1 ሰው ህይወት ደግሞ አልፏል፡፡

በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓት በተደረገ 5015 የላቦራቶሪ ምርመራ ተጨማሪ 137ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸውና የ 1 ሰው ህይወት ማለፉን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታወቁ።

በዚህም እስካሁን በሀገሪቱ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 968 ደርሷል።

ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች 86 ወንዶችና 51 ሴቶች ሲሆኑ፤ የዕድሚያቸውም ከ4 እስከ 75 የዕድሜ ክልል ውስጥ ነው።

ቫይረሱ የተገኘባቸው ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሲሆኑ 109 ሰዎች ከአዲስ አበባ፣ 1 ሰው ከአፋር፣ 2 ሰዎች ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል፣ 17 ሰዎች ከአማራ ክልል እና 8 ሰዎች ከኦሮሚያ ክልል መሆናቸውን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

ከእነዚህም ውስጥ የውጭ የጉዙ ታሪክ ያላቸው 20 ሰዎች፣ ከበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር የታወቀ ግንኙነት ያላቸው 8፣ የውጭ አገር ጉዙ ታሪክና ከበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር የታወቀ ግንኙነት የሌላቸው 109 ሰዎች ናቸውም ተብሏል።

በተጓዳኝ ህመም ምክንያት ህክምና ላይ የነበሩ 62 ዓመት ዕደሜ ያላቸው ወንድ ለኮሮና ቫይረሱ በሽታ በተደረገ የምርመራ ናሙና ከተወሰደ በኋላ የምርመራ ውጤት ሳይደርስ ህይወታቸው አልፏል ብለዋል ሚኒስትሯ።

በዚህም በቫይረሱ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥርም 8 ደርሷል።በሌላ በኩል ተጨማሪ 6 ሰዎች ከቫይረሱ ያገገሙ ሲሆን አጠቃላይ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 197 ደርሷል።

በአጠቃላይ በቫይረሱ ተይዘው በለይቶ ህክምና ውስጥ ያሉ 761 ሰዎች ሲሆኑ በጸና የታመሙ ሰዎች ቁጥር 4 ደርሷል። አጠቃላይ የተደረገ የላቦራቶሪ ምርመራ 101 ሺህ 581 ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም