በአማራ ክልል 3 ሺህ ሄክታር አሲዳማ መሬት በኖራ የማከም ስራ እየተካሔደ ነው

71

ባህርዳር/መተማ / ግንቦት 21/2012  በአማራ ክልል 3 ሺህ ሄክታር አሲዳማ መሬት በኖራ በማከም ምርታማነቱን እንዲጨምር የማድረግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ። 

የቢሮው የአፈር ለምነት ባለሙያ አቶ አጠቃ አይቸው ለኢዜአ እንደገለጹት በአሲዳማነት የተጎዳ የእርሻ መሬትን አክሞ ምርታማነቱን ለማሳደግ 60 ሺህ ኩንታል ኖራ በማቅረብ ጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋል ።

እስከ አሁን 17 ሺህ 528 ኩንታል ኖራ ለአርሶ አደሮች በማሰራጨት በ5 ሺህ 170 ሄክታር የእርሻ መሬት ላይ ተበትኖ ለዘር ዝግጁ ሆኗል ።

ቀሪውን የኖራ ምርት ከደጀንና ከኦሮሚያ ክልል ጫንጮ የማጓጓዝ ስራ እየተከናወነ ሲሆን እስከ ሰኔ ወር አጋማሽ ሙሉ በሙሉ ለአርሶ አደሮች ይሰራጫል።

የኖራ ምርት ብክነትን ለመቀነስም ሳይንሳዊ አሰራሩን ተከትሎ በመስመር ከዘር ጋር ጥቅም ላይ እንደሚውል ለማድረግም እየተሰራ ይገኛል።

የእርሻ መሬቱን አክሞ ምርታማነቱን ለማሻሻል እየተሰራ ያለው ተግባርም በኮሮና ምክንያት የምርት መቀነስ እንዳይከሰት የሚደረገው ጥረት አካል ነው ብለዋል።

በአንድ ሄክታር የእርሻ መሬት ላይ እስከ 20 ኩንታል የኖራ ምርት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው በኖራ የታከመ አሲዳማ መሬት ምርታማነትን በእጥፍ ለማሳደግ ያስችላል።

 ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ አሲዳማ መሬታቸውን በማከም የሰብል ምርታማነቱን ማሳደግ እንደቻሉ የተናገሩት ደግሞ በደቡብ ጎንደር ዞን ፋርጣ ወረዳ የማይነት ቀበሌ አርሶ አደር ሰንደቄ አወቀ ናቸው።

ባለፈው ዓመት በሩብ ሄክታር መሬት 10 ኩንታል ኖራን ከኮምፖስት ጋር ቀላቅለው በመጠቀም  አልምተው 80 ኩንታል ድንች ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

መሬቱ በኖራ ከመታከሙ በፊት 15 ኩንታል ድንች ብቻ ያገኙበት እንደነበር ገልፀዋል ።

በወረዳው የሳህርና ቀበሌ አርሶ አደር አለቃ ማረው ባየ በበኩላቸው ኖራ የሚያስገኘውን ጥቅም በመረዳት አሲዳማ መሬታቸው በማከም ምርታማ አድርገውታል ።

በዚህም ከሩብ ሄክታር መሬት የሚያገኙትን የስንዴ ምርት ከ3 ኩንታል ወደ 10 ኩንታል፣ ገብስ ደግሞ ከ2 ወደ 6 ኩንታል ማሳደግ እንደቻሉ አስረድተዋል

በዘንድሮው የመኽር ወቅትም በሩብ ሄክታር መሬት ለሚያለሙት የስንዴ ሰብል 7 ኩንታል ኖራ ገዝተው በሚያለሙት ማሳ ላይ መበተናቸውን ጠቅሰዋል።

በክልሉ ባለፈው ዓመት ከ22 ሺህ ኩንታል በላይ የኖራ ምርትን በመጠቀም 1 ሺህ 700 ሄክታር መሬት በተለያየየ የሰብል ዘር መሸፈን እንደተቻለ ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም