በግንቦት 20 ድል ድልድዮችና መንገዶች ቢሰሩም የፍቅር፣ ሰላምና አንድነት መንገዶች ግን ፈርሰዋል- ኦባንግ ሜቶ

73

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20/2012 (ኢዜአ) በግንቦት 20 ድል ድልድዮችና መንገዶች ቢሰሩም የኢትዮጵያውነት ፍቅር፣ ሰላምና አንድነት መንገዶች ግን እንዲፈርሱ ብዙ የተለፋበት መሆኑን የሰብዓዊ መብት አቀንቃኙ ኦባንግ ሜቶ ተናገሩ።

"እለቱ የብሔር ብሔረሰቦችን መብት ያስከበረ ነው" ተብሎ በብሔራዊ የድል በዓልነት መከበር የለበትምም ብለዋል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ኦባንግ ሜቶ የግንቦት 20 በዓልን በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል።

በንግግራቸውም በግንቦት 20 ድል ድልድዮችና መንገዶች ቢሰሩም የኢትዮጵያዊነት ፍቅር፣ ሰላምና አንድነት መንገዶች እንዲፈርሱ መደረጉን ተናግረዋል።

በመሆኑም ግንቦት 20 ብዙ ጊዜ የሚወሳበት የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት ሲወራ የነበረውን ያክል አልተተገበረም ብለዋል።

"ዕለቱ ኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማምጣት ባደረጉት ትግል የተገኘ ውጤት ቢሆንም ከመነሻው ጀምሮ ለሥልጣንና ለውስን ሰዎች ጥቅም የቆመ የራሱ የሆነ ድብቅ ዓላማ ነበረው" ሲሉ ተናግረዋል።

የልማት ሥራዎች መከወናቸው ዕውን ቢሆንም በተለይ ኢትዮጵያዊነትና በሰላም አብሮ መኖር እሴቶች በከፍተኛ ደረጃ የተሸረሸረበት፣ ሙስና የተስፋፋበት፣ የሰብዓዊ መብት በከፋ መልኩ የተጣሰበት ወቅት ነበር ብለዋል።

እንደ አቶ ኦባንግ ገለጻ ግንቦት 20 ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ በሕዝብ ሥም እየተማለ ተነግዶበታል፣ ብዙዎች ተገድለውበታል፣ ተኮላሽተውበታል፣ አካላቸውም ጎድሏል።

እኩልነታቸው ተጠብቋል የሚባሉ ካሉም የሥርዓቱ አገልጋዮችና በሥልጣን ላይ የነበሩ ጥቂቶች መሆናቸውን አብራርተዋል።

ክልሎችም ቢሆኑ በነፃነት ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ እንዳልነበርና የሚገባቸውንም ጥቅም ሲያገኙ እንዳልነበር ተናግሯል።

በተለይም እንደ ጋምቤላ ያሉ ታዳጊ ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ሥልጣናቸው በተግባር ሲታይ የሚያስተዳድራቸው ሌላ አካል ነበር ብለዋል።

አሁን የመጣውን ለውጥ ለማሰናከል የሚደረገው ሙከራና በተለያዩ አካባቢዎች ለሚከሰቱ ግጭቶች፣ የሰላም መደፍረስ ዋነኛው ምክንያት ከአሁን በፊት የተሰሩ የፖለቲካ ሴራዎች ውጤት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

እነዚህን ችግሮች ለማስተካከልም የረዥም ጊዜ ሥራ ይጠይቃል ብለዋል ኦባንግ።

ግንቦት 20 በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ዴሞክራሲን እውን ለማድርግ ዋጋ የተከፈለበት ዕለት ቢሆንም ለ27 ዓመታት ግን ይህ ሳይሆን አምባገነንነት የሰፈነበት እንደነበር ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም