የዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ ወረርሽኙን ለመከላከል እያከናወናቸው ያሉት ተግባራት አበረታች ነው

358

ሆሳዕና፣ ግንቦት 20/2012 (ኢዜአ) የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ኮሮናን ለመከላከል እያከናወናቸው ያሉ ትተግባራት አበረታች መሆናቸውን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የመሠረተ ልማትና ከተማ ልማት አማካሪ ሚኒስትር አቶ ዣንጥራራ ዓባይ ገለጹ።

የዩኒቨርሲቲው ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት ሚኒስትሩ ተቋሙ  እያከናወናቸው  ያለውን ተግባራት ከባለድርሻ አካላት ጋር የመስክ ምልከታ አድርገዋል።

በዚህ ወቅት እንዳሉት  ዩኒቨርሲቲው የኮሮና ወረርሽን ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ ለችግሩ መፍትሔ ለመስጠት እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት አበረታች ናቸው።

ምቹ የለይቶ ማቆያ ሕንፃዎችና የሕክምና ቁሳቁሶችን ከማዘጋጀት ባሻገር ወረርሽኑን ለመከላከል የሚያግዙ ንጽሕና መጠበቂያ ሳኒታይዘር በማምረት ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት የቫይረሱ ሥርጭት በሀገሪቱ  እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ሆሳዕና ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎችን የምታስተናግድ ከተማ በመሆኗ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የተሻለ መሥራት እንዳለበትም ጠቁመዋል።

ለመማር ማስተማር ሥራው ስኬታማነት በዩኒቨርሲቲው ግቢ እየተከናወኑ ያሉ የመሠረተ ልማት ሥራዎች በአስቸኳይ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲዘጋጁም አቶ ዣንጥራር አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ሀብታሙ አበበ በበኩላቸው ተቋሙ ኮሮና  በሀገሪቱ ላይ የሚፈጥረውን ተፅዕኖ ታሳቢ በማድረግ  ለመከላከልና ለመቆጣጠር የበኩሉን እገዛ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ለችግሩ መፍትሔ እስኪገኝለት ድረስ በምርምር በመታገዝ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

በወረርሽኙ ሳቢያ ወጣቱና አርሶ አደሩ ለችግሩ እንዳይጋለጡ ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

“ከጤና ሚኒስቴር በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የኮቪድ 19 ምርመራ ለማድረግ ዝግጅት ተደርጓል ” ያሉት ደግሞ  የዩኒቨርሲቲው ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶክተር አያኖ ሻንቆ ናቸው።