የጠረፍ ንግድ በመቋረጡ ህገወጥ ንግድ እንዲስፋፋ ምክንያት ሆኗል-የሁመራ ነዋሪዎች

111
ሁመራ ግንቦት 2/2010 በትግራይ ክልል ምዕራባዊ ዞን ከተጎራባች የሱዳን ወረዳዎች ጋር ይደረግ የነበረው የጠረፍ ንግድ በመቋረጡ ህገ ወጥ ንግድ እንዲስፋፋ ምክንያት መሆኑን አስተያየታቸውን የሰጡ የሁመራ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ በኢትዮጵያና ሱዳን ተጎራባች በሆኑ አከባቢዎች ተፈቅዶ የነበረ የ2ሺህ ብር ግምት   የመሰረታዊ ሸቀጥ ልውውጥ ከተቋረጠ አስር አመት የሞላው መሆኑን ነዋሪዎቹ ለኢዜአ ተናግረዋል። በሰቲት ሑመራ ቀበሌ 04 ነዋሪ ወይዘሮ የዝና አረጋዊ እንዳሉት የተለያዩ ሸቀጦችን ወደ ተጎራባች የሱዳን ወረዳዎች በማመላለስ በጠረፍ ንግዱ ተጠቃሚ እንደነበሩ አስታውሰዋል። ጥራጥሬ፣ በርበሬና ቅመማ ቅመሞች ወደ ሱዳን በመውሰድና ከሱዳን  የተለያዩ ለስላሳ መጠጦች፣ ቴሚር፣ ፕላስቲክ ገመድና የልብስ ማጠብያ የዱቄት ሳሙና አምጥተው በመሸጥ በጠረፍ ንግዱ ተጠቃሚ እንደነበሩ ተናግረዋል ። "የጠረፍ ንግዱ ባልታወቀ ምክንያት በመቋረጡ ህገ ወጥ ንግድ እንዲስፋፋ ምክንያት ሆኗል " ያሉት ወይዘሮ የዝና እርሳቸውም ከንግዱ በመውጣታቸው ለችግር መዳረጋቸውን ተናግረዋል ። "የጠረፍ ንግዱ በህዝቦች መካከል የባህል ትስስር ፈጥሮ ነበር" ያሉት ደግሞ ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ አዲሱ አድሐኖም ናቸው፡፡ የጠረፍ ንግዱ በመቋረጡ በዘርፉ ተሰማርተው የነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ወደ ህገ ወጥ ንግድ ስራ መግባታቸውን ጠቁመዋል። የጠረፍ ንግድ ከተፈቀደ ማህበረሰቡ በራሱ ህገ ወጥ የንግድ እንቅሰቃሴን በባለቤትነት የሚከላከል መሆኑን አቶ አዲሱ ተናግረዋል። ነዋሪው አቶ ገብሩ ካህሳይ በበኩላቸው በሑሞራ ከተማ የኮንትሮባንድ ንግድ  እንቅሰቃሴ በአሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ጠቁመዋል። በግል የትራንዚት ማማከር አገልግሎት የተሰማሩ አቶ ተሾመ ሐድጉ በበኩላቸው የጠረፍ ንግድ በመቋረጡ አብዛኛው ህብረተሰብ ደስተኛ አለመሆኑን ተናግረዋል። "ንግዱ ቢፈቀድ ህብረተሰቡ ህገ ወጦችን አሳልፎ በመስጠት ትብብር ያደርጋል " ብለዋል ። በገቢዎች ጉምሩክ ባለስልጣን የሑመራ ጉምሩክ መቅረጫ ጣቢያ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ መለሰ ይማም እንደገለፁት ህገ ወጥ ንግድ እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። ባለፉት ዘጠኝ ወራት 21 ነጥበ 3 ሚሊዮን ብር ግመት ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች በሁመራ በኩል ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ መያዛቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል። ጥራጥሬ ጨምሮ የግብርና ምርቶችና የቁም እንስሳት ደግሞ በህገወጥ መንገድ ወደ ወጭ የሚወጡ መሆናቸው ጠቅሰዋል። የትግራይ ክልል ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዳንኤል መኮንን ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ነዋሪዎች ያቀረቡት አስተያየት ትክክል መሆኑን ተናግረዋል። "የጠረፍ ንግድ በመቋረጡ ለህገ ወጥ ንግድ መስፋፋት በር ከፍቷል" ብለዋል። የተቋረጠውን የጠረፍ ንግድ ለመጀመር የድንበር ንግድ የመገበያያ መጠን ወደ 10 ሺህ ከፍ እንዲልና የንግድ ልውወጥ የሚደረግባቸው ሸቀጦች አይነት እንዲጨምር የሁለቱም አገራት ተጎራባች ክልሎችና ንግድ ሚኒስቴር ስምምነት መድረሳቸውን ገልጸዋል። "ይሁንና በንግድ ሚኒስቴር በኩል ደንቡ ጸድቆ ለክልሎች ባለመላኩ ተግባራዊ ሳይሆን ቆይቷል" ያሉት አቶ ዳንኤል ደንቡ ለክልሎች እንደደረሰ ተግባራዊ እንደሚደረግ አስረድተዋል። ጉዳዩን በተመለከተ የሚመለከታቸውን የንግድ ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች በስልክ  ለማግኘት በተደጋጋሚ የተደረገ ሙከራ አልተሳካም፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም