ኢትዮጵያውያን በሰላም ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ከአገራቱ ጋር በትብብር እየተሰራ ነው— የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

104

አዲስ አበባ ግንቦት 20/2012 (ኢዜአ) በተለያዩ አገራት ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን በሰላም ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ከአገራቱ ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሊባኖስ መንግሥት ጋር በመተባበር በቤይሩት የሚኖሩ 333 ዜጎች ዛሬ አዲስ አበባ እንዲገቡ አድርጓል።

በቀጣይ ቅዳሜ የሚመለሱትን ጨምሮ 649 ኢትዮጵያዊያንን ወደ አገራቸው የሚመለሱ ሲሆን ወደማኅበረሰቡ ከመቀላቀላቸው በፊት የ14 ቀን የግዴታ ለይቶ ማቆያ ውስጥ ይገባሉ ተብሏል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ጺዮን ተክሉ ለኢዜአ እንዳሉት በቤይሩት ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠው የነበሩ 649 ኢትዮጵያዊያን ዛሬና በቀጣይ ቅዳሜ አዲስ አበባ ይገባሉ።

“የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽሕፈት ቤቶች ኢትዮጵያዊያን በሚኖሩባቸው አገራት ደህንነታቸው ተጠብቆ እንዲኖሩ በቅርበት ይከታተላሉ” ብለዋል።

በየትኛውም አገር በነፃነት ሰርተውና ሀብት አፍርተው የመኖር መብታቸው እንዲከበርም በትኩረት እንደሚሰራ ነው ያመለከቱት።

“ከዚህ ጎን ለጎን በሕገወጥ መንገድ ከአገራቸው ወጥተው ሕጋዊ የመኖሪያና የሥራ ፈቃድ የሌላቸው ዜጎች በሰላም ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ከአገራቱ መንግሥታት ጋር በትብብር እንሰራለን” ብለዋል።

ከሊባኖስ የሚመለሱ ዜጎችም ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ለችግር ተጋልጠው እንደነበር ያስታወሱት ሚኒስቴር ዴኤታዋ፣ ወደ አገራቸው እንዲመጡም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።

የሰላም ሚኒስቴር በበኩሉ ከየትኛውም አገር ወደ ኢትዮጵያ የሚመለሱ ዜጎች ደህንነቱ በተጠበቀ የለይቶ ማቆያ ሥፍራ እንደሚቆዩ አመልክቷል።

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ፍሬዓለም ሽባባው እንዳሉት ወደ ኢትዮጵያ ለሚመለሱ ዜጎች ማቆያ የሚሆን በቂ ሥፍራም ተዘጋጅቷል።

“ዛሬ ከሊባኖስ ለተመለሱት ዜጎችም በአዲስ አበባ ሣይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የየራሳቸው መቆያ ክፍል ተዘጋጅቶላቸዋል” ብለዋል።

ተመላሾቹ ከ14 ቀን በኋላ ከለይቶ ማቆያ የሚወጡትም ከኮቪድ-19 ነፃ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ የምሥክር ወረቀት ከጤና ሚኒስቴር ሲመጣ ብቻ መሆኑን አስታውቀዋል።

“ዜጎች በቆይታቸው ምቾት እንዲሰማቸው የሥነ ልቦና አማካሪዎች ተመድበውላቸዋል፤ አስፈላጊ ግብዓቶችም ተሟልተውላቸዋል” ብለዋል።

በሚደረግላቸው የኮቪድ-19 ምርመራ ማንኛውም ሰው ቫይረሱ ከተገኘበት ለተጨማሪ ቀናት እንደሚቆይ ገልጸው፣ ነፃ መሆናቸው ሲረጋገጥ ወደ መኖሪያ ቀያቸው በነፃ ትራንስፖርት የኪስ ገንዘብ ተሰጥቷቸው እንደሚሸኙ አመልክተዋል።