የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ድጋፍ አደረገ

144

ጎንደር፣  ግንቦት 20/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የሰሜን ጎንደር ቅርንጫፍ የኮሮና ቫይረስ ምርመራና ሕክምና በመስጠት ላይ ለሚገኘው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የሰሜን ጎንደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት  ቤት ለሆስፒታሉ  ያደረገው ድጋፍ 80 ሺህ ብር ግምት ያላቸው ፍራሾች፣ ብርድ ልብሶችንና የእጅ ንጽሕና መጠበቂያ ሣሙናዎችን ነው።

የጽሕፈት ቤቱ ላፊ አቶ አታለል ታረቀኝ ዕርዳታውን ለሆስፒታሉ ባስረከቡበት ወቅት እንደተናገሩት ማኅበሩ የበሽታውን ሥርጭት ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ በኩል ከአጋር አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ ነው።

ባለፉት ሁለት ወራትም የጎንደር ዩንቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን ጨምሮ በማዕከላዊ፣ በምዕራብና በሰሜን ጎንደር ዞኖች ለተቋቋሙ የለይቶ ማቆያ ማዕከላት ከ336 ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸው ቁሳቁሶች ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል።

የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አሸናፊ ታዘበው በዕርዳታ ርክክቡ ወቅት እንደተናገሩት ላቦራቶሪው ጎንደር ከተማን ጨምሮ በማዕከላዊ፣ ሰሜንና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች የኮሮና ቫይረስ ምርመራ በማካሄድ ላይ ይገኛል።

ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሉ የኮሮና ናሙና ምርመራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅሰው በቀይ መስቀል የተደረገው ድጋፍም የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል ያግዛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም