በአማራ ክልል ከ4 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ይሰማራሉ

56

ባህርዳር፣ ግንቦት 20/2012 (ኢዜአ) በአማራ ክልል በመጪው ክረምት ከአራት ሚሊዮን በላይ ወጣቶችን በከተማና በገጠር በበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንደሚሰማሩ የክልሉ ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ አባይነህ መላኩ ለኢዜአ እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት በበጎ ፈቃድ ስራ የሚሰማሩ ወጣቶችን ውጤታማነት ለማረጋገጥ የሚያስችል እቅድ እየተዘጋጀ ነው።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የሚከናወነውም በችግኝ ተከላ፣ የኮሮና ቫይረስን  መከላከል፣  የአቅመ ደካሞችና አረጋዊያን ቤትን መጠገን፣ የወባ በሽታን በመከላከልና ሌሎች የልማት ስራዎች በማከናወን ይሆናል ።

በከተማና በገጠር የበጎ ፈቃድ ልማት ስራ  የሚሰማሩ ወጣቶችም  ራሳቸውንና  ቤተሰባቸውን  ከኮሮና ቫይረስ በመጠበቅ እንዲያከናውኑ  የግንዛቤ ፈጠራ  ስራ  በየደረጃው  እንደሚካሄድ ገልጸዋል።

ከኮሮና ቫይረስ መከሰት ጋር ተያይዞም ቀደም ሲል ግማሽ ሚሊዮን በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በማሰለፍ ለህብረተሰቡ የመከላከያ መንገዶችን በማስተማርና አቅመ ደካሞችን በመርዳት አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

ኮሮናን ለመከላከል የሄዱበትን መንገድ፣ ያስገኙት ውጤትና የተገኘውን ተሞክሮ በመቀመር በክረምቱ የበጎ ፈቃድ መርሃ ግብር ራሳቸውን ከኮሮና ቫይረስ በመከላከል ህብረተሰቡን እንዲያገለግሉ ይደረጋል።

የአማራ ክልል ወጣቶች ማህበር ሊቀመንበር ወጣት አባይነህ ጌጡ  በበኩሉ  በክረምት  በሚካሄደው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራ ከ800 ሺህ በላይ አባላቱ በንቃት እንዲሳተፉ ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል ብሏል።

የማህበሩ አባላት በበጎ ፈቃድ ስራው የሚሰማሩት ወጣቶች ራሳቸውን ከኮሮና ቫይረስ አጋላጭ ከሆኑ ነገሮች በመጠበቅ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ የማስተባበር ሚና እንደሚወጡ አስረድቷል ።

በተለይ በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የራስ ዳሽን ተራራን ጨምሮ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የማህበሩ አባላት ከአራት ሚሊዮን በላይ ችግኞችን እንዲተክሉ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ አስረድቷል።

የማህበሩ አባል ወጣት ቴዎድሮስ አደራጀው  እንዳለው   በያዝነው  በጋ በአረንጓዴ  አሻራ  ቀንና በመደበኛው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በባህርዳር የተከሏቸውን ችግኞች በመንከባከብ እያሳደጉ መሆኑን ተናግሯል።

በመጪው ክረምትም "የምንተክላቸውን  ችግኞች ተንከባክበን  ለማሳደግ ራሱን  የቻለ  የተከላ ቦታ እንዲሰጠን ለከተማ አስተዳደሩ ጥያቄ ያቀረብን ሲሆን የአቅመ ደካሞችን ቤት በመጠገንና ግንዛቤ በመፍጠር እንሰራለን" ብሏል።

በክልሉ በ2011 ዓ.ም በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራ ከአራት ነጥብ  አንድ  ሚሊዮን  በላይ ወጣቶች ተሰማርተው የተለያዩ የልማት ስራዎች ማከናወናቸውን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም