በውጭ ሃገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ዜጎችን በሁለት ቀናት ውስጥ የመመለስ ስራ ይጀመራል...ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

62

ግንቦት 20/2012(ኢዜአ) በውጭ ሃገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ዜጎችን በሁለት ቀናት ውስጥ የመመለስ ስራ እንደሚጀመር የሚኒስትሮች ኮሚቴ ሰብሳቢና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

የሚኒስትሮች ኮሚቴ አባላት የኮቪድ- 19 ወረርሽኝን ለመግታት በወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዙሪያ በምስል የተደገፈ የስራ አፈፃፀም ዛሬ ገምግመዋል።

በግምገማቸውም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በሚሲዮኖች ቅንጅታዊ ትብብር ዜጎችን ወደ ሃገር ለመመለስ ዝግጅት በመጠናቀቁ፤ በውጭ ሃገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ዜጎችን በሁለት ቀናት ውስጥ የመመለስ ስራ እንደሚጀመር ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።

ከችግሩ አሳሳቢነት አኳያ በድንበር አካባቢ ተጨማሪ ትኩረት በመስጠት የኳራንቲን አገልግሎት እንዲጠናከር፤ ለበሽታው ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የምርመራ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥንል ተገልጿል።

የወረርሽኙ ስርጭት በአንፃራዊነት ከፍተኛ የሆነባቸው አካባቢዎች ተለይተው ጥብቅ ክትትል እና የጥንቃቄ እርምጃዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ ኮሚቴው አቅጣጫ ማስቀመጡንም ጠቁመዋል።

በተመረጡ የመንግስት ተቋማት፣ የልማት ድርጅቶች እና የግል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የኮሮና-19 ወረርሽን በመከላከል እንቅስቃሴ የመስክ ምልከታ ውጤት ኮሚቴው የተመለከተ ሲሆን አሁንም በየተቋማቱ ከፍተኛ መዘናጋት መኖሩን ገልጸዋል

በቫይረሱ የተጠቁ ወገኖች ቁጥር ከቀን ቀን እየጨመረ በመሆኑ እጅግ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል ያሉት አቶ ደመቀ፤ የጥንቃቄ መመሪያዎቹን በማስተዋል ተግባራዊ ማድረግ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማሳሰባቸውንከፌስቡክ ገጻቸው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም