በመዲናዋ ከ810 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የትምህርት ቤቶችን አቅም እያደገ ነው

91

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20/2012(ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ በ810 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የመንግሥት ትምህርት ቤቶችን አቅም እያሳደገ መሆኑን ገለፀ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ዳኘው ገብሩ ለኢዜአ እንዳስታወቁት ቢሮው የትምህርት ቤቶችን አቅምና ተመራጭነት የሚያሳድጉ ተግባራት እያከናወነ ነው።

በዚህም ከዓለም ባንክ በተገኘ የ750 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ዘመናዊ የማብሰያና መመገቢያ ቤቶች እንደሚገነቡ ገልጸዋል።

እንዲሁም 70 በሚደርሱ ትምህርት ቤቶች ዘመናዊ የመፀዳጃ ቤቶች ግንባታ እንደሚከናወን ተናግረዋል።

በቀጣይ የትምህርት ዘመን በተለይ በግል ትምህርት ቤቶች የሚታየውን ሥርዓተ ትምህርቱን ያለማክበር ችግር ለማስተካከል ጥረት እንደሚያደርግ አቶ ዳኘው አመልክተዋል።

ሌላው የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አዲሱ ሻንቆ በበኩላቸው በትምህርት ቤቶቹ የሚከናወነው ሥራ በወላጆች ዘንድ የሚታየውን የመክፈል አቅም በማገናዘብ ለልጆቻቸው አማራጭ ትምህርት ቤቶች እንዲኖር ያደርጋል ብለዋል።

ሥራው በተያዘው የትምህርት ዘመን ዓመት ከነበረው የመማር ማስተማር ሒደት በመነሳትና ልምድ በመቅሰም እንደሚከናወን ገልጸዋል።

ቢሮው ካለፈው ዓመት የዩኒፎርም ስፌት፣ የጨርቅ ዓይነትና ጥራት እንዲሁም ከምገባ መርሐ ግብር ጋር ልምድ እንዳገኘበት ተናግረዋል።

በከተማው አስተዳደር ከ600ሺህ በላይ ተማሪዎች በዚህ ዓመት ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም