በአበርገሌ ወረዳ ለ181 መምህራን የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ ተሰጠ

104

ሰቆጣ፣ ግንቦት 20/2012 (ኢዜአ ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አበርገሌ ወረዳ ለ181 መምህራን የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ ተሰጠ።

በወረዳው የኒሯቅ ከተማ መሪ ማዘጋጃ ቤት የቅየሳ ባለሙያ አቶ ካላዩ ፍትዊ ለኢዜአ እንደገለጹት የቤት መሥሪያ ቦታ የተሰጠው ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ተደራጅተው ሲጠባበቁ ለነበሩ መምህራን ነው።

በስምንት የቤት ሥራ ማኅበራት ለተደራጁት ለእነዚህ መምህራን መንግሥት ባስቀመጠው መመሪያ መሠረት የመኖሪያ መሥሪያ ቦታ እንዲሰጣቸው ሲጠይቁ መቆየታቸውን አውስተዋል።

ማዘጋጃ ቤቱ ከሦስት ሔክታር በላይ መሬት ከሦስተኛ ወገን ነፃ በማድረግ ለተደራጁ 181 መምህራን የቤት መሥሪያ ቦታ ማስረከቡን ባለሙያው አሰታውቀዋል።

“የመሥሪያ ቦታ ካገኙት መካከልም 52 ሴት መምህራን ናቸው” ያሉት ባለሙያው በቀጣይም ለሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ለመስጠት የቦታ ልየታ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

ለመምህራኑ የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ መሰጠቱ የሀብትና ንብረት ባለቤት በመሆን ተረጋግተው በማስተማር ትውልዱን በዕውቀት እንዲያንጹ  ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ገልጸዋል።

መምህርት ማርታ ግርማ በሰጡት አስተያየት ለቤት መሥሪያ ቦታ እንዲሰጣቸው ለሁለት ዓመታት ያህል ሲጠይቁ ቆይተው አሁን  ምላሽ በማግኘታቸው ደስተኛ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

“በማስተምርበት ኒሯቅ ከተማ  የቤት ኪራይ ወጪ በኑሮዬ ላይ ጫና ፈጥሮብኝ ነበር” ያሉት  መምህርት ማርታ ቦታ በማግኘታቸው በተሰማራሁበት የማስተማር ሥራ በተረጋጋ ሁኔታ እንዳገለግል የሚያበረታታቸው መሆኑን ገልጸዋል።

መምህር ደንበሩ አማረ በበኩላቸው የቤት መሥሪያ ቦታ በመረከባቸው ደስተኛ እንደሆኑ ገልጸው በቦታው  በአጭር ጊዜ መኖሪያ ቤት ለመገንባት የሚያስፈልገውን ዝግጅት ማድረጋቸውንም አመልክተዋል፡፡