በለይቶ ማቆያ ማእከላት የሚገኙ ወገኖች ለቫይረሱ የመጋለጥ ስጋት እንዳሳደረባቸው ገለፁ

267

መተማ፣ ግንቦት 20/2012 (ኢዚአ) ለጤንነታችንና ለደህንነታችን ሲባል ለይቶ ማቆያ እንድንገባ ቢደረግም የማቆያ ማእከላቱ አመቺ ባለመሆናቸው ለቫይረሱ እንዳንጋለጥ ስጋት አድሮብናል ሲሉ በምዕራብ ጎንደር ዞን በአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ የሚገኙ ዜጎች ገለጹ፡፡

 የዞኑ የኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ-ኃይል በበኩሉ የተነሳው ችግር ትክክል  መሆኑን  አምኖ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ለመቅረፍ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።

በመተማ ዮሃንስ የለይቶ ማቆያ የሚገኘው ወጣት አምሳሉ ቢሆነኝ  ለኢዜአ በሰጠው  አስተያየት የለይቶ ማቆያ ማእከሉ በአንድ ክፍል ከ20 በላይ  ሰዎች እንዲኖሩ  መደረጉ  ከበሽታው ተላላፊነት አንጻር ተገቢነት የለውም ብሏል።

“ዛሬ የገባነው ትናንት ከገቡት ጋር ተቀላቅለናል፣ ምንም አይነት ጥንቃቄም  ማድረግ  አልቻልንም” ያለው ወጣቱ ይህም አንድ ሰው ቫይረሱ ቢኖርበት ወደ ሌላው  የመተላለፍ  እድሉ ሰፊ መሆኑን አስረድቷል።

በተጨማሪም የምግብ፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ፣ የመኝታና የንፅህና  መጠበቂያ ቁሳቁስ  ባለመቅረቡ  ለሌላ ችግር እንጋለጣለን የሚል ፍርሃት አሳድሮብናል ብሏል።

በመሆኑም በለይቶ ማቆያ ቦታዎች ለሚገኙ ዜጎች ለከፋ ችግር እንዳይጋለጡ ተገቢውን የሚመለከተው አካል ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቋል።

ሌላው በመተማ ወረዳ ኮኪት አስገዳጅ ለይቶ ማቆያ የሚገኘው ወጣት ሰሎሞን ዮሃንስ በበኩሉ ለይቶ ማቆያው ቀድሞ ትምህርት ቤት የነበረ ሲሆን በአንድ የመማሪያ ክፍል ውስጥ ከ20 በላይ ሰዎች እንዳሉ ገልፆ ለበሽታው እንዳይጋለጥ እየሰጋ መሆኑን ተናግሯል።

“እስካሁን በቫይረሱ ከተያዙት ሰዎች ውስጥ 27 የሚሆኑት እዚህ ለይቶ ማቆያ መሆናቸውን መረጃው ደርሶናል ያለው ወጣቱ” ይህም ስጋታችን እንዲጨምር አድርጎታል ብሏል።

በማቆያ ቦታዎች የሚስተዋለው ምቹ ያልሆነ አያያዝም ሌሎች ከስደት ተመላሾች በጫካ አቆራርጠው በህገ ወጥ መንገድ እንዲያልፉ እያደረጋቸው መሆኑን አስረድቷል፡፡

በለይቶ ማቆያው ለ28 ቀናት መቆየታቸውን የገለፁት አቶ ሲሳይ ማሞ ደግሞ በለይቶ ማቆያ ቦታዎች ለሚገኙ ዜጎች ተገቢውን ትኩረት እየተሰጠ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዞኑ የኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ-ሃይል ፀሓፊና የዞኑ ማህበራዊ ልማት  መምሪያ  ኃላፊ ሲስተር ክሽን ወልዴ በበኩላቸው በዞኑ የተዘጋጁት የለይቶ ማቆያ  ማእከላት ምቹና  ደረጃቸውን የጠበቁ ባለመሆናቸው ስጋቱ እንዲነሳ አድርጎታል ብለዋል።

ቅሬታ በተነሳባቸው የመተማና ኮኪት የለይቶ ማቆያ ቦታዎች 380 የሚሆኑ ዜጎች እንደሚገኙ ጠቁመው ለእነዚህና በሌሎች ማቆያ ለሚገኙ ዜጎች የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን በተቻለ መጠን ለማቅረብ እየተሞከረ መሆኑን አስረድተዋል።

ከአካባቢው ነባራዊ ሁኔታና ከክልሉ አቅም ውሱንነት የተነሳ የምግብና የመኝታ አቅርቦት  እጥረት መኖሩን ጠቁመው  የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማስተካከል ከክልልና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በመተማ ወረዳ በኮኪት ለይቶ ማቆያ ቦታ 20 ክፍሎች ያሉት ሲሆን በእያንዳንዳቸው  10 ሰው  አካባቢ እንደሚኖር ገልጸው በቀጣይ ችግሩን  ለመቅረፍ ተጨማሪ  ጊዜያዊ  ክፍሎች ለመገንባት ታቅዷል።

ከሱዳን የተመለሱ ዜጎች ለጤንነታቸው ሲባል በለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ቢደረግም ለሌላ ዓላማ እንደመጡ በመቁጠር ተሰባስበው ካርታ መጫወትና ሌሎች ተግባራትን በጋራ በመከወን ለቫይረሱ እንዳይጋለጡ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የኮሮና መከላከል ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ በጉዳዩ ዙርያ በባህርዳር ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያ የምዕራብ ጎንደር ችግር ከአቅም በላይ እየሆነ መጥቷል።

የተነሳውን ችግር ለመቅረፍ ድንኳኖች፣ የውሃ ታንከሮች፣ የውኃ ቦቴዎችና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶች ወደ አካባቢው መላኩን ጠቁመው በቀጣይም ከፌደራል መንግስት ጋር በመተባበር ሌሎች ክፍተቶችን ለመሙላት ይሰራል ብለዋል።

በዞኑ ያሉት የለይቶ ማቆያዎች ትምህርት ቤቶች መሆናቸውን  ገልፀው  በቀጣይ  ተጨማሪ  የማቆያ ማዕከላትን ለመገንባት ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ ተመልክቷል።