በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የመስኖና የልማት ስራዎች እየተጎበኙ ነው

202

ደብረ ብርሃን፣ ግንቦት 20/2012 (ኢዜአ)  በደብረ ብርሃን ከተማ 206 የውጭ ሃገራትና የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች በኢንዱስትሪና በሌሎችም ዘርፎች በመሰማራት የአካባቢውን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለማነቃቃት እየሰሩ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።

የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በክልሉ ሰሜን ሸዋ ዞን የመስኖና ሌሎች የልማት እንቅስቃሴዎችን እየጎበኙ ነው። 

የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ደስታ አንዳርጌ በጉብኝቱ ወቅት እንደተናገሩት ባለሃብቶቹ 15 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ሲሆን ከ23 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎችም የስራ እድል እየፈጠሩ ይገኛሉ።


በአካባቢው እየታየ ያለው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ መስፋፋት ለወጣቶች ከሚሰጠው የስራ እድል ባለፈ የተለያዩ ክህሎቶችን እንዲያዳብሩ እንደሚያደርግም አስረድተዋል።

የከተማ አስተዳደሩም ከዚሁ ጎን ለጎን ወጣቶችን በማደራጃት በ358 ሄክታር መሬት በከተማ ግብርና በመስኖ ልማት እንዲሳተፉ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የዞኑ ግብርና መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ መሰረት ሃይሌ በበኩላቸው ከደብረብርሃን ከተማ በተጨማሪ በዞኑ በዚህ የበጋ ወራት 29 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ መልማቱን ተናግረዋል።

ከለማው መሬትም 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እስከ አሁን 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል መሰብሰብ መቻሉን አስረድተዋል።

በክረምቱ ወቅትም በቆላማ አካባቢዎች በይፋት ቀጠና 500 ሺህ የቡና ችግኝ ለተከላ መዘጋጀቱን አመልክተዋል።

የማንጎና ሌሎች ተክሎችን ደግሞ በእንሳሮ፣ መርሃ ቤቴና ሚዳ ወረዳ ለማልማት ስራ መጀመሩን ገልፀዋል።

ጉብኝቱ ከደብረ ብርሃን ባለፈ በዞኑ በባሶና ወራና ወረዳ ጎሽ ባዶ ቀበሌ በአንድ የሆላንድ ባለሃብት እየተካሄደ ያለ የዶሮ እርባታ፣ በአንጎለላ ጠራ ወረዳ ጫጫ ከተማ በጥቃቅንና አነስተኛ የስራ ዘርፎች ተደራጅተው ወደ ስራ የገቡ የወጣቶችን የስራ እንቅስቃሴም ያካተተ እንደሆነ ተገልጿል።

በጉብኝቱ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ብናልፍ አንዷለምን ጨምሮ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪና ሌሎች የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም