የብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ሊግ ስብሰባ እየተካሄደ ነው

142

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20/2012 (ኢዜአ) የሊጉ ሥራ አስፈጻሚዎች ስብሰባ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚሁ መድረክ ላይ የአጋር ፓርቲዎችን ጨምሮ ውህደት የፈጸሙ ፓርቲዎች እየተሳተፉበት ነው።    

የፓርቲው ሴቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ መስከረም አበበ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ እንዳሉት፤ ስብሰባው የሊጉን ሕገ ደንብ፣ፕሮግራምና የአሰራር መመሪያዎች ተወያይቶ ያጸድቃል።

እንዲሁም ሴቶች ለኮሮና ቫይረስ ተጋላጭነታቸውን ለመቀነስ የጋራ አቅጣጫ ማስቀመጥና በአረንጓዴ ልማት ላይ ተሳትፎአቸውን ማጎልበት ላይ ይወያያል ብለዋል።  

ሴቶች ከአረንጓዴ ልማት ጋር በተያያዘ ሚናቸውን እየተጫወቱ መሆናቸውን ያነሱት ወይዘሮ መስከረም፤ ባለፈው ዓመት ተካሄደው የችግኝ ተከላ ላይ ጉልህ አሻራ እንዳሳረፉ አስታውሰዋል።  

ሊጉ በመጪው ክረምት ሴቶችን በማስተባበር ሁለት ቢሊዮን ችግኞች ለመትከል እየተዘጋጀ መሆኑን ኃላፊዋ አስታውቀዋል።

በየደረጃው ያለው ጽህፈት ቤት ችግኞቹ የሚተከሉትበትን ቦታና አፈጻጸም ተከታትሎ እንዲያስፈጽም አቅጣጫ መቀመጡን አመልክተዋል።   

 የኮሮና ቫይረስ ሴቶች ተጋላጭነትን ለመቀነስ ሊጉ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የተናገሩት ወይዘሮ መስከረም፤በዚህም አቅመ ደካማ ሴቶችን በማገዝ፣ራሳቸውንና አካባቢያቸውን ከቫይረሱ እንዲጠብቁ ግንዛቤ ይፈጠራል ብለዋል።

እንዲሁም በደም እጥረት የሌሎችን ሕይወት ለማትረፍ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።   

ፓርቲው ወደ ውህደት ከመምጣቱ በፊት በተለይ የአጋር ፓርቲዎች ሴቶች ተሳትፎ ተገድቦ እንደነበር ያሉት ኃላፊዋ፣ ውህደቱ በሊጉ ውስጥ የተሻለ የአንድነት መንፈስ መፍጠሩን ተናግረዋል።

ሥራ አስፈጻሚዎቹ ከስብሰባው በተጓዳኝ የችግኞች እንክብካቤ ያደርጋሉ።በደም ልገሳ መርሐ ግብር ላይ እንደሚሳተፉ ተገልጿል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም