በአምቦ ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ 439 ወገኖች ድጋፍ ተደረገ

113

አምቦ፣ ግንቦት 20/2012 (ኢዜአ) በአምቦ ከተማ ተማሪዎችን ጨምሮ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ 439 ወገኖች የትምህርት መከታተያ ሬዲዮ ፣ ምግብ እና ንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደረገ።


ከ555 ሺህ  ብር ግምት ያላቸው ቁሳቁሶቹን ድጋፍ ያደረጉት “ስታንድ ፎር ቨርነረብል” እና የኢትዮጵያ ወንጌላዊ ቤተክርስቲያን መካነየሱስ ማዕከላዊ ምዕራብ ሸዋ ሲኖዶስ  የተባሉ ድርጅቶች ናቸው፡፡

የስታንድ ፎር ቨርነረብል ድርጅት ዳይሬክተር አቶ ምስጋናው ኢቲቻ  ትናንት  በአምቦ ከተማ ተገኝተው  ከ350 ሺህ 498 ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገዙ ሬዲዮኖችን በችግር ምክንያት ትምህርታቸውን መከታተል ላልቻሉ 232 ተማሪዎች በነፍስ ወከፍ አበርክተዋል።

ሬዲዮኖቹ በጸሐይ እና ኤሌክትሪክ ኃይል እንዲሁም በባትሪ ድንጋይ  የሚሰሩ “ፍላሽ” ተቀባይ መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

ድጋፉ በህጻናት ልማት ፕሮጀክቶች ስር ለታቀፉት ተማሪዎች ትምህርት እንዳያመልጣቸው  ከሬዲዮው በፍላሽ በመቅረጽ ጭምር እንዲከታተሉ የሚያስችላቸው ነው፡፡


ድርጅቱ በተጨማሪም  የተለያዩ የንጽህና መጠበቂያ  ቁሳቁሶች ለተማሪዎቹ ድጋፍ አድርጓል፡፡

ከዚህም ሌላ የኢትዮጵያ ወንጌላዊ ቤተክርስቲያን መካነየሱስ ማዕከላዊ ምዕራብ ሸዋ ሲኖዶስ በዝቅተኛ  የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ 207  ወገኖች ከ205 ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸው የንጽህና መጠበቂያና የምግብ እህል ድጋፍ አበርክቷል፡፡


የሲኖዶሱ ፕሬዝዳንት ቄስ ተሬሳ ፉፋ እንዳሉት ለነዚህ ወገኖች የተበረከተው ድጋፍ 104 ኩንታል በቆሎ፣207 ሊትር ዘይት፣104 ሊትር ሳኒታይዘርና 1ሺ242 የልብስ ሳሙና ነው፡፡


በተጨማሪም ለአምቦ ከተማ ጤና ጽህፈት ቤት  70 ሊትር አልኮል፣ 20 ፓኬት የአፍንጫና አፍ መሸፈኛ ጭንብል እንዲሁም  50ፓኬት የእጅ ጓንት ድጋፍ ማድረጋቸውንም ጠቁመዋል፡፡

የአምቦ ከተማ አስተዳደር ኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ሰብሳቢና የአስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ሳህሉ ድርብሳ ድርጅቶቹ ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

በተለይ ተማሪዎቹ የተሰጣቸውን የትምህርት መከታተያ መሳሪያ በአግባቡ እንዲጠቀሙበትም አሳስበዋል፡፡


ድጋፍ ከተደረገላቸው ተማሪዎች መካከል ተማሪ ኩማ ዳባ በሰጠው አስተያየት ድርጅቱ ባደረገለት የሬዲዮ ድጋፍ  እንደሌሎች ተማሪዎች ትምህርቱን በመከታተል ጠንክሮ እንደሚማር ገልጿል፡፡


ተማሪ አርጊቱ ምስጋና በበኩሏ በድርጅቱ ድጋፍ ስትማር መቆየቷን ጠቅሳ  “ትምህርቴን በተሰጠኝ ሬዲዮ ተጠቅሜ እከታተላለሁ “ብላለች፡፡

ሌላው ድጋፍ የተደረገላቸው በአምቦ ከተማ የወዴሳ ቀበሌ ነዋሪ አካል ጉዳተኛ  ወይዘሮ መርጌ ነጋ በሰጡት አስተያየት “ተሽከርካሪ ጋሪ (ዊልቸር) ላይ ተቀምጬ በየመንደሩ በመሄድ ጸጉር ሰርቼ ነበር የምኖረው ፤አሁን በበሽታው ምክንያት ስራውን በማቆሜ  ተቸግሬያለሁ”  ብለዋል።

ለተደረገላቸውም ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።