በአማራ ክልል የኮሮና ቫይረስን የመከላከል ስራው ለማጠናከር የማስተካከያ አማራጮች ቀረቡ

90

ባህርዳር፣  ግንቦት 20/2012 (ኢዜአ) በአማራ ክልል የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የተከናወነው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ የባህሪ ለውጥ ማምጣት ስላልተቻለ የማስተካከያ አማራጮችን ለመጠቀም መዘጋጀቱን የክልሉ የኮሮና መከላከልና መቆጣጠር ግብረ ሃይል አስታወቀ።

ህብረተሰቡ ስለኮሮና ቫይረስ ያለውን እውቀት፣ ግንዛቤና የባህሪ ለውጥ በማምጣት ያለበትን ደረጃ ለመለካት የሚያስችል ሳይንስን መሰረት ያደረገ ጥናት መካሄዱን ግብረ ኃይሉ ገልጿል ።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊና የግብረ ሃይሉ ሰብሳቢ ዶክተር ሙሉነሽ አበበ እንደገለጹት በአገራችን የኮሮና ቫይረስን ከመከላከል ውጭ ሌላ አማራጭ የሌለ መሆኑን በማመን ወደ ስራ ተገብቷል።

የክልሉ ግብረ ሃይል በስሩ ስምንት ኮሚቴዎችን በማዋቀር የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እስካሁን ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ማከናወን መቻሉን አውስተዋል።

ከተሰራው መካከልም በተለያዩ ሚዲያዎች፣ በኪነ ጥበብና ሌሎች የማስተማሪያ ዘርፎች ህብረተሰቡን በተከታታይነት የማስተማር ስራ በመሰራቱ ስለ ኮሮና ያለው ግንዛቤ እየጨመረ መጥቷል።

ይሁን እንጂ ህብረተሰቡ ባለው እውቀት ልክ ችግሩ እኔንም ሆነ ሌላውን ቤተሰቤን አደጋ ላይ የሚጥል ነው ብሎ በማመን ራሱን ከቫይረሱ አጋላጭ መንገዶች በመጠበቅ በኩል የባህሪ ለውጥ አለመምጣቱን ተናገረዋል።

በዚህም አሁን ላይ በክልሉም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በፍጥነት እየጨመረ በመምጣቱ የእያንዳንዱን ቤት ለማንኳኳት ተቃርቧል ብለዋል።

ግብረ ሃይሉም እስካሁን የተጓዘበትን የማስተማርና የመከላከል ዘዴ በመገምገም መልካም ተሞክሮዎችን ለማስቀጠል፣ ችግሮችን ለማረምና አዳዲስ ሃሳቦችን በመጨመር በአዲስ መልክ ለመስራት መወሰኑን ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደርና የኮሮና መከላከል ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ በበኩላቸው ህብረተሰቡ ስለኮሮና ቫይረስ ያለውን ግንዛቤ ለመለካት በሳይንሳዊ መንገድ ጥናት ተካሂዷል።

በናሙና ተወስደው በጥናቱ ከተካተቱት በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ውስጥ 81 በመቶ የሚሆኑት ስለ ኮሮና በቂ ግንዛቤ እንዳላቸው የገለጹ ቢሆንም እነሱንም ጭምር እንደሚያጠቃ  የሚያስቡት ግን 29 በመቶ ብቻ ናቸው ብለዋል።

የጥናቱ ግኝት እንደሚያሳየውም ህብረተሰቡ ስለኮሮና ቫይረስ አደገኛ በሽታ መሆኑን ጠንቅቆ ቢያውቅም ለራሱና ለሌላው ማህበረሰብ ጥንቃቄ በማድረግ በኩል ሰፊ ክፍተት አለ ብለዋል።

ይህም ምንም እንኳ በቂ እውቀትና ግንዛቤ ቢኖረውም ባወቀው ልክ የባህሪ ለውጥ በማምጣት ራሱንም ሆነ ሌላውን ከመከላከል አንጻር ቁርጠኝነት የጎደለው መሆኑን ማረጋገጥ ይቻላል ብለዋል።

ይህን መሰረታዊ ችግር ለመቅረፍም በሚዲያ ከሚሰጠው ትምህርት በተጨማሪ መልዕክቶችን በካሴት በመቅረጽ በአንቡላንስና ሌሎች መኪኖች ማይክራፎን በመግጠም የማስተማር ስራ በአዲስ መልክ ተጀምሯል።

በተጨማሪም የበጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በማሰማራት ህብረተሰቡን እንዲያስተምሩ እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመው ህዝቡም ከተከለከሉ ድርጊቶች ራሱን በመጠበቅ ህይወቱን እንዲያተርፍ አሳስበዋል።  

መንግስት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጉ የኮሮና በሽታ ለህዝቡና ለአገር አደገኛ መሆኑን በመገንዘቡ ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ጠቅላይ አቃቤ ህግና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሴክሬታሪያት አቶ ገረመው ገብረ ጻድቅ ናቸው።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተደነገጉ እገዳዎችንና ክልከላዎችን ይዘት ለህብረተሰቡ የሚያስተምርና ህግ ለማስከበር   እስከ ታችኛው  የአስተዳደር  እርከን  አደረጃጀት  ተዘርግቶ  እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ከአሁን በኋላ ግን ከበሽታው መስፋፋት አንጻር ሲታይ እያወቁም ሆነ ሳያውቁ የተጣለውን አዋጅና ማስፈጸሚያ ደንቡን የሚጥሱ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል።

በአማራ ክልል በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ40 በላይ መድረሱ የባህሪ ለውጥ ላለመምጣቱ አንዱ ማሳያ መሆኑን ከግብረ ሃይሉ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም