ለመዲነዋ ወጣቶች ከ2 መቶ ሺህ በላይ የሥራ ዕድል ተመቻችቷል

678

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20/2012 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ የሥራ ዕድል ፈጠራና ልማት ኢንተርፕራይዝ ባለፉት አስር ወራት ብቻ ከ2መቶ ሺህ ለሚልቁ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን አስታወቀ።

የኢንተርፕራይዙ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚኪያስ ሙሉጌታ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው 229 ሺህ 46 ዜጎች መካከል 82 ከመቶ በላይ ወጣቶች ሲሆኑ፣ 9 ነጥብ 5 የሚሆኑት አዲስ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሩቋን ናቸው።

የኢንተርፕራይዙ የአስር ወራት ክንውንም በእቅድ ከተያዘው 110 ከመቶ እንደሆነም አመልክተዋል።

የሥራ ዕድል የተፈጠረባቸው የሥራ ዘርፎችም ማኑፋክቸሪንግ፣ ኮንስትራክሽን፣ የከተማ ግብርና፣ ንግድ፣ የአገልግሎት ዘርፍ እና የሥራ ቅጥር መሆናቸውንም አቶ ሚኪያስ ጠቁመዋል።

የሥራ ዕደሉ ከተመቻቸላቸው ውስጥ ከ52 ሺህ ለሚልቁት ሥራ ፈላጊዎች ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ጋር በመተባበር በተለያዩ የሙያ መስኮች ስልጠና መሰጠቱንም አስረድተዋል።

በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ 18 ሺህ 100፣ በኮንስትራክሽን 18 ሺህ 436፣ በከተማ ግብርና 6 ሺህ 803፣ በአገልግሎት ዘርፍ 43 ሺህ 862፣ በንግድ 31 ሺህ 944 እንዲሁም በቅጥር 107 ሺህ 459 የሥራ ፈላጊዎቹ ወደ ሥራ ገብተዋል።

ኢንተርፕራይዙ ከዚህ በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ መጨረሻ 219 ሺህ 386 ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሥራ ዘርፉንና የሥራ አጡን በመለየትና በአንድ ቋት የመመዝገብ ሥራ መከናወኑንም አቶ ሚኪያስ አስረድተዋል።

ከነዚህ ሥራ ፈላጊዎች መካከል 119 ሺህ 391 ወንዶች፣ 99 ሺህ 993 ሴቶች ሲሆኑ፤ 78 ከመቶው  ወጣቶች ናቸው።

በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 የሚገኘው የአብይና ሚኪያስ የልብስ ስፌት ድርጅት በማንፋክቸሪንግ ዘርፍ የሥራ ዕድሉን ባገኙ ወጣቶች የተቋቋመ ነው።

የድርጅቱ የሽያጭና የዕቃ አቅርቦት ኃላፊ አቶ አብይ ጌቱ እንደሚናገረው፤ ከ1 አመት በፊት ወደ እዚህ የሥራ ዘርፍ ሲገቡ አራት ሆነው በ25 ሺህ ብር ካፒታል እንደነበር ያስታውሳል።

አሁን ላይ 10 ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠራቸውም በላይ ካፒታላቸው ወደ 3 መቶ ሺህ ማደጉን ተናግረዋል።

የዚሁ ድርጅት መስራችና ባልደረባ የሆነችው ወይንሸት አስማማው በበኩሏ በተፈጠረው የሥራ ዕድል ቤተሰቦቻቸውን በበቂ ሁኔታ ከማስተዳደር አልፈው አሁን ላይ ሥራውን ሲጀምሩ ከነበራቸው 3 የልብስ ስፌት ማሽን ወደ 10 ማሳደግ መቻላቸውን ታስረዳለች።

የድርጅቱ ባለቤቶች የጉለሌ ክፍለ ከተማም ሆነ ወረዳው ከፍተኛ እገዛ እያደረገላቸው እንደሆነ ገልጸው፤ ድርጅታቸውን ለማስፋፋት ግን የፋይናንስ አቅርቦት ችግር እንቅፋት እንደሆነባቸው ያስረዳሉ።

በተጨማሪም የሰለጠነ የሰው ሃይል ማግኘቱም አንዱ ፈተና እንደሆነ የሚናገሩት ወይንሸትና አብይ፤ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት በልብስ ስፌት የሰለጠኑ ባለሙያዎችን ቢያቀርብ የሥራ ዕድሉ እንዳለ ይገልጻሉ።

ሚሊዮን ኃይሌና ጓደኞቹ በከተማ ግብርና ዘርፍ የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸው በዶሮ እርባታ የሚሠሩ ወጣቶች ናቸው።

የማኅበሩ መስራች የሆነው ወጣት ሚሊዮን ኃይሌ እንደሚናገረው፤ በተፈጠረላቸው የሥራ ዘርፍ አምስቱም ጓደኞቹ ተጠቃሚ መሆናቸውን ይናገራል።

በሥራ ፈጠራው 400 ሺሕ ብር ካፒታልና 45 ካሬ ሜትር የዶሮ ማርቢያ  ቦታ እንደተሰጣቸው የሚናገረው ወጣት ሚሊዮን 500 ዶሮዎችን ገዝተው እንቁላል እየሸጡ በፊት ተቀጥረው ያገኙት ከነበረው ገቢ ሦስት እጥፍ እያገኙ እንደሆነም ገልጿል።

ይሁን እንጂ ሥራቸውን አስፋፍተው ገቢያቸውን ለማሳደግ የቦታ ችግር እንዳለባቸው ይናገራሉ።

የሥራ ዕድል ለተፈጠረላቸው ዜጎች ድጋፍና ክትትል የሚሰጠው የወረዳ 8 የሥራ ዕድል ፈጠራ ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊው አቶ ደሳለኝ ኃይሉ ተቋማቱ ላነሷቸው ችግሮች እንዳሉ ተናግረዋል።

የልብስ ሰፌቱ ዘርፍ በተነሳው የካፒታል ጥያቄ ከተዘዋዋሪ ፈንዱ ጋር ተያይዞ ያለ ችግር መሆኑን ጠቅሰው፤ የተዘዋዋሪ ፈንዱ ችግሮች ሲፈቱ ችግሮቻቸው አብረው እንደሚፈቱ ተናግረዋል።

በዶሮ አርቢ ወጣቶቹ የተነሳው የቦታ ጥያቄ በከተማው ካለው የቦታ ችግር አንፃር በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመፍታት እንደሚያስቸግር አቶ ደሳለኝ ተናግረዋል።

በተፈጠረላቸው የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንደሆኑ የሚናገሩት የሥራ ዕድል ተጠቃሚዎቹ ወጣቱ ሥራ ሳይንቅ በመደራጀት መንግሥት በሚፈጥረው የሥራ ዕድል እንዲጠቀም ጥሪ አቅርበዋል።