በወጭና ገቢ ንግድ ላይ ትልቁን ሚና እየተወጡ ላሉት ድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች ድጋፍና ትብብር እንዲደርግ ተጠየቀ

123

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 20/2012(ኢዜአ) በኢትዮጵያ ወጭና ገቢ ንግድ ሎጀስቲክስ አገልግሎት ላይ ትልቁን ሚና እየተወጡ ለሚገኙ የድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች ህብረተሰቡ ድጋፍና ትብብር እንዲያደርግ ተጠየቀ።

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በመከሰቱና በተለይ ደግሞ በአጎራባች አገሮች ቫይረሱ እየተስፋፋ መምጣቱን ተከትሎ ድንበር ተሻጋሪ የጭነት አሽከርካሪዎች ላይ መገለል እየደረሰባቸው መሆኑ እየተነገረ ነው።።

በዚህም የትራንስፖርት ባለስልጣን ከኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሰሪዎች ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር በድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች ላይ የሚስተዋለውን የመገለል ችግር ለመፍታት የግንዛቤ ስራ ማከናወን ጀምሯል።

የግንዛቤ መፍጠር ስራው ከድሬዳዋ የተጀመረ ሲሆን በአይሻ ደወሌ መስመር እስከ ጅቡቲ በሚያዘልቀው መስመር ላይ በቀጣዮቹ ቀናት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑም ታውቋል።

በቅስቀሳውም በአገሪቱ በወጭና ገቢ ሎጀስቲክስ አገልግሎት የተሰማሩ የጭነት አጓጓዥ አሽከርካሪዎችን ማህበረሰቡ ክብር በመስጠትና በማገዝ እንድተባበራቸው ተጠይቋል።

ድንበር እያቋረጡ የግብርና፣ ኢንዱስትሪና የግንባታ ግብዓቶችን በማመላለስ የአገሪቱን ኢኮኖሚ በማንቀሳቀስ የአሽከርካሪዎቹ ሚና ትልቅ መሆኑም ተመልክቷል።

የእነርሱ ስራ በተለያዩ ምክንያቶች የሚስተጓጎል ከሆነ በአገሪቱ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ላይ የሚፈጥረው ጫና ቀላልባለመሆኑ፤ 

በተለይ ድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች በሚያርፉባቸው ቦታዎች ህብረተሰቡ ከጎናቸው እንድቆምና ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጣቸው ተጠይቋል።

አስከፊውን ጊዜ በትብብርና በመተጋገዝ ማለፍ እንደሚገባም ተጠቁሟል።

ባለፈው ዓመት ተገንብቶት አገለግሎት መስጠት የጀመረው የድሬዳዋ-አይሻ-ደወሌ የፍጥነት መንገድ የአዋሽ-ሚሌ-ሰመራ-ጋላፊ መንገድን በመተካት እንደ አማራጭ መንገድ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም