በሽሬ እንዳስላሴ ኢቨስትመንትን የሚያጠናክር የመግባቢያ ስምምነት ተፈረመ

111

ሽረ እንዳስላሰ (ኢዜአ) ግንቦት 19 ቀን 2012 ዓ ም በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ አየጨመረ የመጣውን የኢንቨስትመንት ፍሰት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማገዝ የከተማው አስተዳድርና የትግራይ ኢንቨስትመንትና ኤክስፖርት ኮሚሽን የመግባቢያ ስምምነት ዛሬ ተፈራረሙ። 

ስምምነቱን የተፈራረሙት የሽሬ እንዳስላሴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ተስፋይ ጸጋይና የትግራይ ክልል ኢንቨትመንትና ኤክስፖርት ኮሚሽን ዳሬክቶሬት ዳሬክተር አቶ ጎይተኦም ገብረህይወት ናቸው።

የኮሚሽኑ ዳይሬክተር አቶ ጎይተኦም ገብረህይወት ስምምነቱን ከተፈራረሙ በኋላ እንደገለጹት አላማው በሽሬ እንዳስላሴ ለኢንቨስትመንት ቦታ የወሰዱ ባለሀብቶችን  ድጋፍና ክትትል ለማድረግ ነው ብለዋል።

ባለሃብቶቹ የወሰዱትን መሬት በአግባቡ በውላቸው መሰረት እንዲያለሙት ድጋፍና ክትትል ለማድረግ የሚያግዝ ስምምነት መሆኑንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል ።

የከተማ አስተዳደሩ ከሁለት ወር በፊት አስፈላጊውን የመሰረተ ልማት አውታሮች አማልቶ ባዘጋጀው የኢንዱስትሪ ዞን 52 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ውል ገብተው መሬት ተረክበዋል ።

የተወሰደውን መሬት ባለሀብቶቹ በአግባቡ እንዲያለሙት ለማገዝ ከመንግስት የተሟላ የአንድ መስኮት አገልግሎት የሚያገኙበት አሰራር ያቀፈ ስምምነት መሆኑንም ዳይሬክተሩ ገልፀዋል ።

  ለባለ ሃብቶች የተፈቀደውን የኢንቨስትመንት ማትግያ የማስፈፀም ፣ የገበያ ትስስር የመፍጠርና የግንባታ ሂደታቸውን መከታተል  የስምምነቱ አካል ናቸው ተብሏል ።

ይህ ሁሉ ድጋፍና የቅርብ ክትትል የሚደረግላቸው ባለሃብቶች በውላቸው መሰረት ወደ ልማት የማይገቡ ከሆነ የወሰዱትን መሬት ተወስዶ ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ የማድረግ ውክልና ለከተማ አስተዳደሩ የሰጠ ስምምነት ጭምር መሆኑንም አስረድተዋል ።

የሽሬ እንዳስላሴ ከተማ አስተዳደር  ከንቲባ አቶ ተስፋይ ጸጋይ በበኩላቸው ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ 3 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ካፒታል ያስመዘገቡ 52 ባለሀብቶች  በዚሁ የስምምነት ማእቀፍ እየተመሩ ተጠቃሚዎች አድል መፈጠሩን ገልፀዋል ።

የኢንቨስትመንት መሬቱን ለግንባታ አመቺ  ለማድረግም ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ አስፈላጊ መሰረተ ልማቶች እንዲሟሉ መደረጉን ከንቲባው አስረድተዋል ።

ባለሀብቶቹ በማኑፋክቹሪንግ፣ በኮንስትራክሽን፣ በሪል ስቴትና በሌሎች የኢንዱስትሪ ዘርፎች የሚሰማሩ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

ስምምነቱ የመንግስት ልዩ ልዩ አገልግሎት በአንድ የመስኮት ማእከል እንድናገኝ ይረዳናል ያሉት ደግሞ  የኢንቨስትመንት መሬት ከወሰዱ ባለሀብቶች መካከል ወይዘሮ አልማዝ በርሔ ናቸው ።

ሌላው በሰነድ ስምምነቱ የተገኙት ባለሃብት አቶ ከማል አብደልዋስዕ በበኩላቸው የከተማ አስተዳድሩና የኢንቨስትመንት ኮሚሽኑ የስምምነት ሰነድ መፈራረማቸው የኢንቨስትመንት ፍሰቱንና አገልግሎቱን የተሳለጠ ያደርገዋል ብለዋል።