ሃርላዎች የከተሜ አመጋገብ ባህል ነበራቸው -ጥናት

191

አዲስ አበባ ግንቦት 19/2012 (ኢዜአ) በምስራቁ ኢትዮጵያ ሀረር አካባቢ  የኖሩት ሃርላዎች ዘመናዊ የኑሮ  ዘይቤ እንደነበራቸው ሄሪቴጅ ዴይሊ  ድረገጽ ዘገበ።

የቅርስ ጥናት ተመራማሪዎች በኢትዮጵያ ባደረጓቸው ቁፋሮዎች በሺዎች የሚቆጠሩ የእንስሳት አጥንቶችን ማግኘታቸውን ሲገልጹ ኢትዮዽያውያኑ ከግብፅ ፣ ከሕንድ እና ከአረብ ሃገራት ጋር የነበራቸው የንግድ ልውውጥ ዘመናዊ የሚያስብል ነው።

በኤክስተር ዩኒቨርሲቲ እና በኢትዮዽያ ባህልና ቅርስ አስተዳደር ባለስልጣን ባለሙያዎች በምስራቅ ኢትዮዽያ በሚገኙ ሶስት ጣቢያዎች ላይ የተከናወኑ ቁፋሮዎች አሳዩ እንደተባለው በአካባቢው በ 12 ኛው ክፍለዘመን ሰዎች ይኖሩ እንደነበር የሚያመላክቱ መስኪዶችና የመቃብር ስፍራዎች ተገኝተዋል።

 ቡድኑን በሚመሩት የዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ቶማስ ኢንሶል እና የአረብ እና ኢስላማዊ ጥናቶች የአርኪኦሎጂ ባለሙያ ጄን ጋስትራ በሐረር እና በገንዳ ሀርላ በተደረገው ቁፋሮ በአፍሪካ መጀመሪያ የሆኑት ማስረጃዎች ተገኝተዋል ብለዋል።

ቀደም ሲል በፕሮፌሰር ኢንሶል የተደረጉት ቁፋሮዎች መስጊዶቹን እና የመቃብር ስፍራዎችን ከማሳየታቸውም በተጨማሪ   በቻይና እና በግብፅ ተሰርተው ወደ ሃርላ የመጡ ቅንጡ የመመገቢያ ቁሳቁሶች እንዲሁም ከቀይ ባህር የተለቀሙ ጨሌዎችና ጌጥ የተጨመረባቸው የእንጨት ስራዎች ተገኝተዋል ፡፡

ተመራማሪዎቹ ሀርላ እስልምና ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣቱ በፊት በ6ኛው እና በ7 ኛው ክፍለዘመን እንደተመሰረተችና  በ15 ኛው ክፍለዘመን በአካባቢው በተከሰተው በወረርሽኝ  በአካባቢ ለውጥ ምክንያት እና እስልምና ሲስፋፋ ተጨማሪ የእርሻ መሬት ለማግኘት በሚል ምክንያት ልትፈርስ እንደቻለች ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

እንደተመራማሪዎቹ ገለጻ ከሆነ የአካባቢው ነዋሪዎች እስካሁን ያልተገኙ ትንንሽ መስጊዶችን ይጠቀሙ የነበረ ሲሆን የሙስሊም ማህበረሰቡ ቁጥር እያደገ ሲሄድ ትልልቅ የመስኪድ ሕንፃዎችን ገንብተዋል ብለዋል ፡፡

በጥንታዊው የማህበረሰቡ በመኖሪያ አካባቢዎች እና በሥራ ቦታዎችም ይሄንን ያህል ጥራት እና ብዛት ያላቸው አጥንቶች አግኝተው እንደማያውቁ የተናገሩት ፕሮፌሰር ኢንሶል አጥንቶቹ በጥሩ ሁኔታ ላይ ያሉ ስለሆኑ ለማስረጃነት የሚኖራቸው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው ባይ ናቸው።

 ግኝቱ በአካባቢው ይኖሩ ስለነበሩ ሰዎች ሃይማኖታዊ ማንነት አዲስ መረጃ መሆኑን የሚናገሩት ፕሮፌሰሩ የአካባቢው ሰዎች ሁሉንም አይነት ሃይማኖቶችን ከመከተል ይልቅ እስልምናን አብልጠው የመረጡበትን መንገድ ያሳያል ብለዋል  ፡፡

በአጥንቶቹ ላይ የተደረገው ትንታኔ እንደሚያመለክተው ከሆነ የቀንድ ከብቶችን ለእርሻ ስራ እና እህል ለማፍጨት ግመሎች ፣ ፈረሶች እና አህዮችን ደግሞ የንግድ እቃዎችን እና ሌሎች ምርቶችን ለማጓጓዝ ይጠቀሙ ነበር ያለው ዘገባው የእንስሳቱ አጥንቶች ዕድሜ መረጃ ትንተና ደግሞ ላሞችን ከማረድ ይልቅ እስከ 3 አመታት በማቆየት ወተታቸውን የመጠቀም ልማድ እንደነበረ ጠቅሷል።

በእስልምና ሃይማኖት ለምግብነት የተከለከለው አሳማ አጥንቱ በአካባቢው የተገኘ መሆኑን ያነሱት ተመራማሪዎቹ የአካባቢው ነዋሪዎች የእስልምና ተከታዮች ቢሆኑም ከሌሎች ማህበረሰቦች ጋር በፈጠሩት ሁለንተናዊ መስተጋብር እና ጎብኚዎችና የተጎራባች አካባቢዎች ሰዎች የአሳማ ስጋ እንዲመገቡ ስለማስቻሉ ያስረዳሉ።

የእስልምና ሃይማኖት ማእከል ተደርጋ በምትወሰደው ሐረር በተደረጉ ምርምሮች ምንም አይነት የአሳማ አጥንት ያለመገኘቱ ለዚህ አስረጂ ሊሆን እንደሚችል ያነሱት ተመራማሪዎቹ በአካባቢው የነበረው የእስልምና መስፋፋት ልማዱን ሊገታው ችሏል ብለዋል።

አፍሪካ አርኪዎሎጂ መጽሄት ላይ የታተመው ጥናት ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት የነበረው የአመጋገብ ስርአት የእንስሳት አጠቃቀም የመጓጓዣ ስርአቶች የየአካባቢዎቹን ሃይማኖትና አጠቃላይ የአኗኗር ዘይቤ ለማሳየት ትልቅ ጠቀሜታ አለው ተብላል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም