በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 20 ባለሃብቶች ያላለሙትን መሬት እንዲመልሱ ተወሰነ

79

አሶሳ፣ ግንቦት 19/ 2012( ኢዜአ)  በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዝቅተኛ አፈጻጸም ያሳዩ 20 ባለሃብቶች ለኢንቨስትመንት የተረከቡትን ስምንት ሺህ 400 ሄክታር የሚጠጋ መሬት እንዲመልሱ ተወሰነ፡፡
የክልሉ አካባቢ መሬት አስተዳደር እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ገለታ ኃይሉ  እንደገለጹት ቢሮው በአሶሳ፣ ባምባሲ፣ ዳንጉር እና ሌሎችም ወረዳዎች የባለሃብቶችን እንቅስቃሴ ገምግሟል፡፡

በግምገማው በእርሻ እና እጣን ኢንቨስትመንት ስምንት ሺህ 400 ሄክታር የሚጠጋ መሬት የተረከቡ 20 ባለሃብቶች ችግሮች እንደታዩባቸው አመልክተዋል፡፡

ባለሃብቶቹ ከታዩባቸው ችግሮች መካከል የተረከቡትን መሬት ሳያለሙ ማስቀመጥ፣ በገቡት ውል መሠረት ወደ ስራ አለመግባት እና ሌሎች የአፈጻጸም ችግሮችም እንዳለባቸውም ጠቅሰዋል፡፡

የክልሉ ኢንቨስትመንት ቦርድ ይህንኑ መረጃ መሠረት በማድረግ  የተሰጣቸውን መሬት እንዲመልሱ ውሳኔ ማስተላለፉን አስታውቀዋል፡፡

ሌሎች 11 ባለሃብቶች ደግሞ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው አቶ ገለታ ተናግረዋል፡፡

ባለሃብቶቹ የወሰዱት ብድር እና ከቀረጥ ነጻ ያስገቧቸው ንብረቶችን ለማስመለስ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር የሚደረግ ጥረት መኖሩንም አመልክተዋል፡፡

በሌላ በኩል በክልሉ የኢኮኖሚ ዞን የሆነ  ከ56 ሺህ ሄክታር በላይ  መሬት ለአልሚ ባለሃብቶች መዘጋጀቱን ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡

ባለፉት ሶስት ዓመታት ተከስቶ ከነበረው የጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞ  ኢንቨስትመንት መስተጓጎል  እንደነበር አስታውሰው "በአሁኑ ወቅት ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆነ አስተማማኝ ሠላም አለ "ብለዋል፡፡

ቢሮው አሰራሩን ለማሻሻል እና ከሙስና የጸዳ ለማድረግ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ጥረት እያደረገ መሆኑን አቶ ገለታ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም