በትግራይ 329 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ እየተከፋፈለ ነው

51

መቐለ፣ ግንቦት 19 /2012 ዓ.ም (ኢዜአ) በትግራይ ክልል ለዘንድሮው የመኽር አዝመራ አገልግሎት የሚውል 329 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ወቅቱን ጠብቆ ለአርሶ አደሩ እየተከፋፈለ መሆኑን የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮ የአዝርእት ልማትና የአፈር ለምነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ገብረስላሴ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት በመኽሩ የእርሻ ስራ ለክልሉ 680 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ያስፈልጋል ።

329 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ከወደብ ተጓጉዞ  ወደ ክልሉ በመድረሱ ለአርሶ አደሮች እየተከፋፈለ ሲሆን ቀሪው ደግሞ በዚህ ወር ውስጥ ሙሉ በሙሉ ወደ ክልሉ እንደሚደርስ ተናግረዋል ።

እስከ አሁን ድረስ ወደ ወረዳዎች ተጓጉዞ በመከፋፈል ላይ ከሚገኘው ማዳበሪያ 141 ሺህ ኩንታል በእጅ ለእጅ ሽያጭ የተከፋፈለ ነው ተብሏል ።

በክልሉ ለመኽር አዝመራው 16ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር እንደሚያስፈልግ የገለፁት ዳይሬክተሩ 10ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር በእጅ ያለ ሲሆን ቀሪው ከምርጥ ዘር አባዢ ኢንተርፕራይዞች  በግዢ ለመሙላት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል ።

በዘንድሮው የመኽር አዝመራ በክልሉ 1ነጥብ 3 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።

ዘመናዊ ማዳበሪያ መጠቀም ከጀመሩ ከአምስት አመታት በላይ  ማስቆጠራቸውን  የገለጹት ደግሞ ትግራይ ደቡባዊ ዞን የእንዳመኾኒ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ሕሉፍ በላይ ናቸው።

አንድ ሄክታር በሚሆን የእርሻ መሬታቸው ማደበሪያ ተጠቅመው የሚዘሩት ሰብል  የስምንት ኩንታል ብልጫ ያለው ምርት እንዳገኙ  ያለፉት አመታትን በአብነት መጥቀስ  ተናግረዋል።

የማዳበሪያ ጠቀሜታ በመገንዘብ ዘንድሮም ሁለት ኩንታል ገዝተው ማዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

በትግራይ ደቡባዊ ምስራቅ ዞን የሕንጣሎ ወጀራት ወረዳ የአራ -ዓሰገዳ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ዕቋር ሓዱሽ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት ስለ ዘመናዊ ማዳበሪያ አስፈላጊነት አብዛኛው አርሶአደር አውቆታል ብለዋል።

አርሶ አደሩ ለመከሩ የእርሻ ስራ ሶስት ኩንታል ማዳበሪያ እንዲመጣላቸው ክፍያ ፈፅመው በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም