ቤተ ክርሲትያኗ ለ150 ችግረኛ ዜጎች በቋሚነት የምግብ ድጋፍ ማድረግ ጀመረች

107

ዲላ ግንቦት 19/2012 (ኢዜአ) የዲላ መብራት ኃይል አጥቢያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርሲቲያን በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ለተቸገሩ 150 ዜጎች በቋሚነት የምግብ ድጋፍ ማድረግ ጀመረች።

ቤተ ክርስቲያኗ በመጀመሪያ ዙር ለአንድ ወር የሚሆን ፉርኖ  ዱቄትና የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማስክ  ዛሬ ድጋፍ አድርጋለች።

የቤተክርስቲያኗ ሰብሳቢ አቶ መስፍን አለማየሁ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ የወረርሽኙን መከሰት ተከትሎ ለችግር የሚዳረጉ ወገኖችን ለመታደግ ታስቦ የተደረገ ድጋፍ ነው ።

ድጋፉም በቤተሰብ ቁጥር ከ10 እስከ 20 ኪሎ ግራም ፉርኖ ዱቄትና በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ እራሳቸውን ከቫይረሱ እንዲጠብቁ የሚረዳ የአፍና የአፈንጫ መሸፈኛ ጭንብል ያካተተ መሆኑን ተናግረዋል።

የኮሮና ቫይረስ ከእለት ወደ እለት ስርጭቱ እየጨመረ መምጣት አስደንጋጭ ከመሆኑም ባለፈ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ በሚገኙ ወገኖች ላይ ጫናው እየበረታ እንደሚሄድ ጠቁመዋል።

ይህንን ጫና ለማቃለል ድጋፉ በቋሚነት በየወሩ ለመስጠት ቤተክርስቲያኗ የፍቅርና ሪህራሄ አገልግሎት ዘርፍ በማቋቋም ድጋፍ ማድረግ መጀመሯን ሰቢሳቢው ገልፀዋል ።

ድጋፉ የተለያዩ አካላትን በማስተባበር የተሰባሰብ ሲሆን፤ ለመጀመሪያው ዙር ከ36 ሺህ ብር በላይ ወጪ ተደርጓል ።

ድጋፍ ከተደረገላቸው ዜጎች መካከል ወይዘሮ ሸምስያ ቶፊቅ በሰጡት አስተያየት ያለ ምንም የሃይማኖት ልዩነት የተደረገው ድጋፍ ደስታ እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።

በዚህ አስቸጋሪ ወቅት በቋሚነት የምግብ ድጋፍ በማግኝታቸው ጭንቀታቸውን ስላቃለለላቸው ቤተክርስቲያኗን  አመስግነዋል።

የዲላ ከተማ የኮሮና መከላከል ግብረ ሃይል  አባልና የኢንተርፕራይዝና ስራ እድል ፈጠራ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ዳንኤል ደምሴ የቫይረሱን ስርጭት ከመከላከል ጎን ለጎን ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን ማሰብ የሁሉም አካላትኃላፊነት ሊሆን ይገባል ብለዋል ።

የቤተክርስቲያኗ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ የከተማው አስተዳደር የተቸገሩ ወገኖችን ለመድረስ የሚያደርገውን ጥረት ከመደገፍ ባለፈ ኢትዮጵያዊ መረዳዳትን በተግባር የሚያሳይ በጎ ተግባር ነው ብለዋል ።