በጨረታ ለግብይት የሚቀርቡ እቃዎች ለኮሮና ቫይረስ አጋላጭ ሆነዋል

195

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19/2012 ዓ.ም ( ኢዜአ) በጨረታ ለግብይት የሚቀርቡ እቃዎች ለኮሮና ቫይረስ አጋላጭ መሆናቸው ተጠቆመ፡፡

እቃዎች ለግብይት የሚቀርቡበትና ከተለያዩ ቦታዎች የሚመጡ በርካታ ተገበያዮችን በአንድነት የሚያገናኘው ‘ጨረታ አስኮ’ ለኮሮናቫይረስ አጋላጭ የሆነ ጥግግትና ንክኪ እየተስተዋለበት ነው።
በገበያው እየሰሩ ያሉ ማህበራት ”ሳንሰራ መብላት አዳጋች ስለሆነብን በረሃብ ከመሞት በሚል የተቻለንን ጥንቃቄ እያደረግን እየሰራን ነው” ይላሉ።

የአካባቢው አስተዳደርም ከነገ ጀምሮ እቃዎች በፈረቃ እንዲሸጡና ግብይቶች ርቀታቸውን ጠብቀው እንዲካሄዱ ከማህበራቱ ጋር መስማማቱን ገልጾ፤  ይህ ካልሆነ ግን የሚካሄደው ንግድ እንዲቋረጥ የሚደረግ መሆኑን ገልጿል።

የጨረታ ግብይት በርካቶች በአንድነት ተሰብስበው እቃ ተጫርተው የሚሸጡና የሚገዙበት ቦታ በመሆኑ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ሰዎችን በአንድነት የሚያሰባስብ ነው።

በተለምዶ “ጨረታ አስኮ” እየተባለ የሚጠራው አካባቢ የተለያዩ አልባሳትና ጫማዎች ለግብይት የሚቀርቡበት የግብይት ቦታ ነው።

በርካቶች የተለያዩ ፈጣን ምግቦችን በመስራት፣ ለገበያተኛው እያቀረቡ የሚተዳደሩበት የንግድ ቦታም ጭምር ነው።

በገበያ ቦታው የእጅ መታጠቢያ ተዘጋጅቶ ተገበያዮች እየታጠቡ እንዲገቡ ቢደረግም የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል አካላዊ ርቀትን መጠበቅ ግድ በሆነበት በዚህ ወቅት በገበያ ቦታው ላይ ንክኪ ይስተዋላል። 

በገበያ ቦታው ተደራጅተው ከሚሰሩት ጫኝና አውራጆች መካከል አንዱ የሆነው ወጣት ያሬድ አያሌው እንደሚናገረው፤ በጨረታ ገበያ እየሠራ የሚተዳደር አብዛኛው ሰው ኑሮው ከእጅ ወደ አፍ ነው፡፡

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ ለአንድ ወር ያህል ስራ በመተዋቸው ኑሮ ከብዷቸው እንደነበር አስታውሷል።

ይህን ችግር ለማለፍ ከማህበራቸው ድጋፍ መደረጉን ጠቅሷል።

የኮልፌ አካባቢ አጫራቾች አክሲዮን ማህበር የቦርድ አመራር የሆኑት አቶ መስፍን ስጦታው በበኩላቸው በገበያ ማዕከሉ ሲሰሩ የነበሩ ሰዎች ከመጋቢት 7 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ስራቸውን በፈቃደኝነት አቋርጠው እንደነበር አስታውሰዋል።

በመሆኑም አብዛኛው ሰው ኑሮውን በእለት ገቢ ስለሚደግፍ በስራው መቋረጥ ለተቸገሩ ማህበሩ ለአባላቱ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

‘ድጋፉ ዘላቂ መሆን ስለማይችል በገበያው የሚሰሩ ሰዎች በምን መልኩ ይስሩ’ የሚለውን ከወረዳው ጋር በመነጋገር ተጨማሪ ቦታ በአቅራቢያው ተሰጥቷቸው እየተሰራ እንደሆነም ገልጸዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ አሁንም የሚቀር ነገር ቢኖርም በተቻለ መጠን ጥንቃቄ እየተደረገ ግብይቱ እየተፈፀመ መሆኑንም ተናግረዋል።

ሆኖም ተገበያዩ ርቀቱን እንዲጠብቅና እጁን በሚገባ እንዲታጠብ የሚሰጡ ምክሮችን ችላ የማለት አዝማሚያ እየተስተዋለበት መሆኑንም አልሸሸጉም።

የአካባቢው አስተዳደር ከዚህ ቀደም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እንደተከሰተ በታወቀበት ጊዜ በገበያው ከሚሰሩ ማህበራት ጋር በመነጋገር ስራ እንዲቋረጥ ቢደረግም በእለት ገቢ የሚተዳደሩ ሰዎች ባቀረቡት ጥያቄ በድጋሚ ግብይቱ እንዲጀመር መደረጉን ገልጿል።

በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ የወረዳ 15 ምክትል ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ከበደ እንደገለጹት፤ ወረዳው የኮሮናቫይረስ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ለመቀነስ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ 1 ሺህ ያህል ነዋሪዎች ድጋፍ አድርጓል።

የኮሮናቫይረስን ወረርሽኝን ለመከላከልም ሰዎች የሚበዙባቸው ግሮሰሪና ጠመጥ ቤቶች እንዲዘጉ መደረጉንና ሆቴልና ሬስቶራንቶችም ርቀት በመጠበቅ አገልግሎት እንዲሰጡ ክትትልና ድንገተኛ ፍተሻ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በወረዳው ህዝብ ከሚበዛባቸው ቦታዎች አንዱ በሆነው የጨረታ ገበያ ውስጥ ከሚሰሩ ማህበራት ኮሚቴዎች ጋር በመነጋገር ግብይቱ ተዘግቶ እንደነበር አስታውሰዋል።

ነገር ግን በእለት ገቢ የሚተዳደሩ ሰዎች ባቀረቡት ቅሬታ አስፈላጊውን የጥንቃቄ ርምጃ በመውሰድ ስራው ዳግም መጀመሩን ገልጸዋል።

በወቅቱ የጨረታ እቃዎች በፈረቃ ለግብይት እንዲቀርቡና አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ ግብይቱ እንዲፈፀም ከስምምነት ላይ ቢደረስም እየተካሄደ ያለው ግብይት ስምምነቱን የተከተለ እንዳልሆነ የወረዳው አስተዳደር መመልከቱን ተናግረዋል።

ይህ አሰራር የሚተገበር ካልሆነ የኅብረተሰቡን ጤና መጠበቅ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር በመሆኑ ገበያው አሁንም ሊዘጋ እንደሚችል ጠቁመዋል።

በትናንትናው እለት ከማህበራቱ ኮሚቴዎች ጋር ወረዳው ባደረገው ውይይት እቃዎች በፈረቃ ቀርበው ግብይቱ እንዲፈፀምና አስተባባሪዎችም በተገበያዮች መካከል ርቀት እንዲጠበቅ እንደሚያደርጉ መስማማታቸውን አቶ መስፍን ተናግረዋል።

ገበያው መዘጋቱ የግድ ከሆነ በዚህ ሳቢያ ለጉዳት ለሚጋለጡ የወረዳው ነዋሪዎች ድጋፍ የሚደረግ መሆኑንና ሌሎች አቅም የሌላቸውንም ከኮሚቴዎች ጋር በመሆን ተለይተው ከሚኖሩበት አካባቢ አስተዳደር ጋር በመነጋገር፣ የሚደገፉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ወረዳው ጥረት ያደርጋል ብለዋል።

ኢዜአ በጨረታ ገበያው ተገኝቶ ባደረገው ምልከታ ወደ ጨረታው የሚገቡ ሁሉ እጃቸውን የሚታጠቡና ማስክ የሚያደርጉ ቢሆንም አካላዊ ርቀትን ያለመጠበቅ የጎላ ችግር መኖሩን ታዝቧል።