በወልዲያ ከተማ ኮሮናን ለመከላከል 17 ሺህ 200 ቤቶችን ያዳረሰ ልየታ ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
በወልዲያ ከተማ ኮሮናን ለመከላከል 17 ሺህ 200 ቤቶችን ያዳረሰ ልየታ ተካሄደ
ወልዲያ/ ደብረማርቆስ ግንቦት 19/2012( ኢዜአ ) በወልዲያ ከተማ የኮሮና ወረርሽኝ ስጋትን ለመከላከል 17 ሺህ 200 ቤቶችን ያዳረስ የልየታ ስራ መካሄዱን የከተማው ኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ገለጸ።
በሌላ በኩል በደብረ ማርቆስ መናኽሪያ ከትናንት ጀምሮ መንገደኞች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል እንዲጠቀሙ እየተደረገ መሆኑም ተመልክቷል።
የወልዲያ ከተማ ግብረ ኃይሉ ጸሐፊ አቶ ፈንታው ስጦታው ለኢዜአ እንዳሉት በአካባቢው ከሚያዚያ ወር መጨረሻ እስከ ግንቦት 17/2012ዓ.ም የቤት ለቤት ልየታ ስራ ተከናውኗል።
በቤት ለቤት አሰሳውም 26 ቡድን የያዘ የጤና ባለሙያዎችና በጎ ፈቃደኞች ተሳትፈዋል።
በዚህም 17 ሺህ 200 ቤቶችን ያዳረስ የልየታ ስራ በማካሄድ ለ76 ሺህ 350 ሰዎችን የሙቀት መለካት ስራ ተደራሽ ማድረግ እንደተቻለ ተናግረዋል።
የሰውነት ሙቀት መለካት ስራው በከተማው መግቢያ ሶስት በሮች በሚገኙ የዶሮ ግብር፣ የጀነቶ በርና የጎንደር በር ጤና ጣቢያዎች ለአንድ ወር ተኩል የተካሄደ ነው።
በሂደቱ የተገመቱ 20 ግለሰቦች በለይቶ ማቆያ ሆነው በተደረገላቸው ምርመራም ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው መረጋገጡን አስረድተዋል።
አቶ ፈንታው ማህበረሰቡ ከሌላ አካባቢ የሚመጡና ምልክት የታየባቸውን ሰዎች በመጠቆም ትብብር እያደረገ ነው ብለዋል።
በከተማው የቀበሌ አራት የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያ ወይዘሮ ብርቱካን ደጉ በበኩላቸው በቤት ለቤት አሰሳው ህብረተሰቡ ተባባሪ እንደነበር ተናግረዋል።
በአሰሳው ወቅትም በበሽታው አስከፊነት ልክ ህብረተሰቡ የወጡ የመከላከያ መንገዶችን እየተገበረ እንዳልሆነ መመልከታቸውንና ይህ እንዲስተካከልም የግንዛቤ ትምህርት መስጠታቸውን አስታውቀዋል።
የከተማው ነዋሪ አቶ ወሰን ሽፈረው በሰጡት አስተያየት የቤት ለቤት አሰሳው በተወሰነም ቢሆን ስጋታቸው እንቀነሰላቸው ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በደብረ ማርቆስ መናኽሪያ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ከትናንት ጀምሮ መንገደኞች የአፍ ና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል እንዲቀሙ እየተደረገ መሆኑን የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አባልና የከተማው መንገድና ትራንፖርት ጽህፈት ቤት አመልክቷል።
የጽህፈት ቤቱ የመናኽሪያ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ቡድን መሪ ወይዘሮ ታሪክ ሞላ ለኢዜአ እንደተናገሩት ቫይረሱን ለመከላከል ሲባል በመናኽሪያው ማስክ ሳይለብሱ መግባት አይቻልም።
ማንኛውም ተሳፋሪም ሆነ አገልግሎት ፈልጎ ወደ መናኽሪያው የሚሄድ ግለሰብ ጭንብል መጠቀም የግድ መሆኑን አስታውቀዋል።
ይህም የቫይረሱ ስርጭት እየጨመረ በመምጣቱና ህብረተሰቡ ቫይረሱን ለመከላከል የሚያሳየው ጥንቃቄ የጎደለው እንቅስቃሴ ከግምት በማስገባት ነው።
ማህበረሰቡ ጭንብል ሳይለብስ ከመናኽሪያው ግቢ እንዳይገባ የትራንስፖርት ማህበራትና የፀጥታ አካላት በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በጭንብል ከሚጠቀሙ መንገደኞች መካከል ወይዘሮ ትጋረድ ዳኛው በሰጡት አስተያየት መንግስት መንገደኛው የአፍና አፍንጫ መከላከያ እንዲለብስ በማድረግ እየወሰደ ያለው ጥንቃቄ የሚበረታታ ነው ብለዋል።
ከዚህ በፊት ቫይረሱን በመፍራት ለመልበስ ሞክረው ቤተሰቦቻቸው ሳይቀሩ ተሳልቀውባቸው እንደነበር አስታውሰዋል ።
አሁን በመናኽሪያው መተግበሩ በሽታውን ለመከላከል ያግዝል፤ በበሽታው እያዛለሁ ከሚል ስጋትም ያስቀራል ብለዋል።
አቶ ያሬድ መለኩ በበኩላቸው በመናኽሪያ ጭንብል እንዲለበስ መደረጉ ጥሩ መሆኑን ገልጸው በመናኸሪያ ውስጥ እጅን በሳሙና የመታጠቡም ሆነ ሳኒታይዘር አጠቃቀም ላይ ክፍተት እንዳለም ጠቁመዋል።
"ስለሆነም የንጽህና ጉዳይ እንደማስኩ ሁሉ ግዳጅ መደረግ ይኖርበታል "ብለዋል።
የደብረ ማርቆስ መናኽሪያ በቀን ከ10 ሺህ የማያንስ የህብረተሰብ ክፍል የሚያስተናግድ እና እስከ 1ሺህ500 ተሽከርካሪዎች ስምሪት እንደሚሰጥበት ተገልጿል።