በቃፍታ ሁመራ ወረዳ 12 ኩንታል አደንዛዥ እጽ ተያዘ - ኢዜአ አማርኛ
በቃፍታ ሁመራ ወረዳ 12 ኩንታል አደንዛዥ እጽ ተያዘ
ሰቲት ሁመራ ግንቦት 19/2012 (ኢዜአ) በትግራይ ክልል ምዕራባዊ ዞን ቃፍታ ሁመራ ወረዳ በተሽከርካሪ ተጭኖ ሲጓጓዝ የነበረ 12 ኩንታል ″ካናቢስ″ የተባለ አደንዛዥ እጽ መያዙን የወረዳው ፀጥታ ዘርፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ገለፁ ።
የጽህፈት ቤት ኃላፊ ሻምበል ሓጎስ ካሕሳይ ለኢዜአ እንደገለጹት ግንቦት 17 ቀን 2012 ዓም በድብቅ ሲጓጓዝ የነበረውን አደንዛዥ እጽ የተያዘው በአካባቢው ሚሊሻና በፖሊስ በተደረገ የተቀናጀ የጋራ ቁጥጥር ነው ።
ስድስት ኩንታል የሚመዘነው ″ካናቢስ″የተባለ አደንዛዥ እጽ የተገኘው በቃፍታ ሁመራ ወረዳ ልዩ ስሙ ″ባህር ሰላም″ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በእርሻ ትራክተር ላይ በተጫነ የውሀ መያዣ ታንከር ውስጥ መሆኑን ገልጸዋል።
አዘዋዋሪዎቹ ለጊዜው የተሰወሩ ሲሆን ለወንጀል አገልግሎት መዋሉን የተጠረጠረው የእርሻ ትራክትር ደግሞ በቁጥጥር ስር እንዲቆይ ተደርጓል ።
ቀሪው ስድስት ኩንታል ደግሞ በተመሳሳይ ጊዜ በወረዳው ″አደባይ″ በተባለ ቀበሌ ህብረተሰቡ ለጸጥታ ሀይሉ በሰጠው ጥቆማ ወደ ሌላ አካባቢ ሊጓጓዝ ሲል ተይዟል ።
የአደንዛዥ እጹ አዘዋዋሪዎች ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ ሁለት ሰዎች በህብረተሰቡ ተሳትፎ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ኃላፊው ተናግረዋል።
አዘዋዋሪዎቹ አደንዛዥ እጽ መሆኑን እንዳይታወቅባቸው 50 ኪሎ ግራም በሚመዝን 12 የፕላስቲክ ከረጢት ከፋፍለው እንደቋጠሩትም ኃላፊው ገልፀዋል ።