በአንበጣ መንጋ ሰብላቸው ለተጎዳባቸው አርሶ አደሮች የምርጥ ዘር ድጋፍ ተደረገ

89

ደሴ (ኢዜአ) ግንቦት 19/2012  በምስራቅ አማራ "ቀለም ኢትዮጵያ" የተሰኘ መንግስታዊ ያልሆን የልማት ማህበር በአንበጣ መንጋ ሰብላቸው ለወደመባቸው አርሶ አደሮች 330 ኩንታል ምርጥ ዘር ድጋፍ አደረገ ። 

በማህበሩ የሰሜን ምስራቅ አካባቢ ማስተባበሪያ ኮምቦልቻ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኑሩ መሃመድ ለኢዜአ እንደገለፁት ማህበሩ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በመከላከልና በተለያዩ የልማት ስራዎች እየተሳተፈ ህብረተሰቡን እያገለገለ ይገኛል፡፡

ምርጥ ዘሩ እየተከፋፈለ ያለው በምስራቅ አማራ ተከስቶ በነበረው የአንበጣ መንጋ የሰብል ምርታቸውን ሙሉ በሙሉ ለወደመባቸው 6 ሺህ አርሶ አደሮች ነው ።

ለደቡብ ወሎና ሰሜን ወሎ አርሶ አደሮች እየተሰራጨ ያለው ምርጥ ዘር የማሽላ፣ ማሾ፣ በቆሎና ሽምብራ ሰብሎች ያካተተ ነው፡፡

ለምርጥ ዘር ግዥ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉንም ኃላፊው ተናግረዋል ።

እስካሁንም በቃሉ ወረዳ ለሚገኙ 980 አርሶ አደሮች 80 ኩንታል ምርጥ ዘር የተሰራጨ ሲሆን ቀጣይ በአርጎቦ፣ ወረባቦ፣ ተሁለደሬና ሀብሩ ወረዳዎች በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ይሰረጫል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ለአንበጣና ጸረ ተባይ ኬሚካል መርጫ የሚሆኑ 133 የመርጫ መሳሪያዎችን ለማሰራጨት በ250 ሺህ ብር ግዥ ተፈፅሟል ።

በደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ ይመር ሰይድ እንደገለፁት  ከሰኔ 2011 ጀምሮ በዞኑ በተከሰተው የአንበጣ መንጋ በመኸርና በበልግ በ5 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በለማ ሰብል ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል።

በተለይም በ2 ሺህ 300 ሄክታር በሚጠጋ መሬት ላይ የነበረ ማሽላ፣ ጤፍ፣ ማሾ፣ በቆሎና ሽምብራ ሙሉ በሙሉ በአንበጣ መንጋው በመውደሙ 11 ሽህ 733 አርሶ አደሮች ለከፋ ጉዳት ተዳርገዋል፡፡

ጉዳቱ  ለአደጋ በመጋለጣቸው ድጋፍ እንዲያገኙ ከፌደራልና ከክልሉ መንግስት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል ፡፡

ማህበሩ የዞኑን የከፋ ችግር አቃልሏል ያሉት አቶ ይመር በተለይ ዘር በተጀመረበት ወቅት በመሆኑ ምስጋናቸውን የላቀ መሆኑን ተናግረዋል ።

ዘር ከቀረበላቸው የቃሉ ወረዳ አርሶ አደሮች መካከል አቶ ከድር ሽኩር በሰጡት አስተያየት ባለፈው መኸር አንድ ሄክታር ከሩብ መሬት ላይ የዘሩት ማሽላና ጤፍ በመንጋው ሙሉ በሙሉ በመውደሙ ለችግር መጋለጣቸውን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የመኽር ዘር የተጀመረ መሆኑን ጠቅሰው ቀለም ኢትዮጵያ ችግራቸውን ተረድቶ 10 ኪሎ ግራም የማሾና ማሽላ ዘር ባደረገላቸው ድጋፍ ወቅቱን ጠብቀው የዘር ስራ መጀመራቸውን ገልፀዋል።

"ቀለም ኢትዮጵያ" በአንድ ሚሊዮን ብር ወጪ በምስራቅ አማራ በኮረና ቫይረስ ምክንያት ለተቸገሩ 1 ሺህ 300 አቅመ ደካሞች በዚህ ወር መጀመሪያ ድጋፍ ማድረጉን መዘገባችን ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም