በወላይታ ዞን ለኮሮና መከላከል ከ17 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተሰበሰበ

61

ሶዶ፣ ግንቦት 19/2012 (ኢዜአ)  በወላይታ ዞን የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ውስጥ ባለሀብቶችና የተለያዩ ተቋማት ከ17 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።

የወላይታ ዞን ምክትል አሰተዳዳሪና የግብረ ሀይሉ ገቢ አሰባሰብ ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ ጎበዜ ጎዳና እንዳሉት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን የመቆጣጠር ስራውን ለማገዝ ባለሃብቱና ህብረተሰቡ በገንዘብና በዓይነት እያደረገ ያለው ድጋፍ የሚበረታታ ነው።


እስካሁን ከዞኑ ከ17 ሚሊዮን ብር በላይ ጥሬ ገንዘብ መሰብሰቡን የጠቆሙት አቶ ጎበዜ በተጨማሪ 7 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የተለያዩ የምግብና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።


በወረርሸኙ ምክንያት አብዛኛው የኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ መቀዛቀዙን ተከትሎ ተጋላጭ የሆኑ ወገኖችን በመለየት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው ብለዋል።

ተጋላጭ ይሆናሉ ተብሎ ከተለዩት ውስጥ የጎዳና ተዳዳሪዎች እንደሚገኙበት ገልፀው፤  በትምህርት ቤት ውስጥ እንዲቆዩ በማድረግ የምግብና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ እየቀረበላቸው መሆኑን ጠቁመዋል።  

በአሁኑ ወቅት እየታየ ባለው ሁኔታ ቫይረሱ የሚገኝባቸው ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል ።

የሙሉጌታ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ባለቤት ሀጂ ሙስጠፋ አወል እንዳሉት ወረርሽኙ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከልና ለመቆጣጠር መንግስት እያደረገ ያለውን ስራ ማገዝ የሁሉም ህብረተሰብ ግዴታ ነው።

ይህንኑ መሰረት በማድረግም በጥሬ ገንዘብ 6 መቶ ሺህ ብር እንዲሁም ግምቱ 5 መቶ ሺህ ብር የሚሆን የንጽህና መጠበቂያ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማዕድ ማጋራት መርሀ ግብር በመቀበል 5 መቶ ሺህ ብር ወጪ በማድረግ በአረካና በሶዶ ከተማ ለሚገኙ ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች ማዕድ ማጋራታቸውን ጠቁመው፤ በቀጣይም አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም