በኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነት ላይ ህብረተሰቡና ምሁራኑ እንዲሳተፉ ተጠየቀ

521

አዲስ አበባ ሰኔ 29/2010 ለኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነት መሻሻል የሁለቱም አገራት ህዝብና ምሁራን እንዲሳተፉ የኢትዮ-ኤርትራ የህዝብ ለህዝብ ግኑኝነት አስተባባሪ ኮሚቴ ጠየቀ።

በሁለቱ አገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ዙሪያ እየሰራ ያለው የኢትዮ-ኤርትራ የህዝብ ለህዝብ አስተባባሪ ኮሚቴ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

ኢትዮጵያ ለኤርትራ የሰላም ጥሪ ማቅረቧን ተከትሎ የኤርትራ መንግስት ወደ አዲስ አበባ ልዑካን ቡድን መላኩ የሚታወስ ነው።

በኮሚቴው የኢትዮጵያ አስተባባሪ ኮሚቴ ተወካይ ፕሮፌሰር መድሃኔ ታደሰ እንዳሉት ሁለቱ አገሮች የነበራቸውን ግጭት ወደ ሰላም ለማምጣት የጀመሩት ስራ የአገራቱን ወዳጅነት ወደ ፊት የሚያራምድ ጥሩ ጅማሮ ነው።

የኢትዮ-ኤርትራ ህዝብ በደም፣ በባህል፣ በቋንቋ፣ በታሪክና  በሃይማኖት የተሳሰሩ ቢሆንም ግንኙነታቸው ለ20 ዓመታት ሻክሮ ቆይቷል።

በግጭቱ ሁለቱም ህዝቦች ተጎዱ እንጂ አልተጠቀሙም ያሉት ፕሮፌሰር መድሃኔ ይህን ጥቅም አልባ የጥላቻ ድንበር እንዲወገድ ህዝቡና ምሁራኑ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

በኮሚቴው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ተወካይ አቶ ይሳቅ ዮሴፍ በበኩላቸው በሁለቱም መንግስታት የተጀመረው የመቀራረብና አብሮ የመስራት ፍላጎት ተስፋ ሰጪ ነው ብለዋል።

በሁለቱም አገሮች ዘላቂ ሰላም  ለማምጣት ሁለቱም መንግስታት ከዚህ በፊት የነበሩ ስህተቶች እንዳይደገሙና የሁለቱም አገራት ህዝቦች አሸናፊ የሚሆኑበትን አሰራር እንዲከተሉ ጠይቀዋል።

የህዝቡ ለህዝብ ግንኙነቱ የሁለቱም አገራት መንግስታት ድጋፍ ታክሎበት ተቋማዊ የሆነ ግንኙነት መመስረት ያስፈልጋልም ብለዋል።