በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ስርጭት አሳሳቢ እየሆነ ነው

61

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18/2012(ኢዜአ) በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ስርጭት አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ፕሬስ ሴክረተሪያት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ገለጹ።

ኮቪድ 19 ባለፈው መጋቢት ወር በኢትዮጵያ የተከሰተ ቢሆንም በተለይ በግንቦት ወር በእጅጉ እየተስፋፋ መምጣቱን አቶ ንጉሱ ገልጸዋል።

ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች ቫይረሱ የሚገኝባቸው ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱንም ገልጸዋል።

ይህም መንግስትና ህዝብን በእጅጉ እያሳሰበ ነው ብለዋል አቶ ንጉሱ።

የኮቪድ 19 ስርጭት አሁን ላይ ከጋምቤላ ክልል በስተቀር በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተስተዋለ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በተለይ ደግሞ በአዲስ አበባ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የስርጭት መጠኑ እየጨመረ በመሆኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማክበርና መተግበር ይገባል ነው ያሉት።   

"መዘናጋትና ችላ ማለት ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍል በመሆኑ ለመከላከል የጋራ ጥረትና ጥንቃቄ ያስፈልጋል" ብለዋል።

በተለይ ደግሞ የትራንስፖርት አገልግሎት አካባቢዎች፣ የንግድና የገበያ ስፍራዎች እንዲሁም የአምልኮ ስፍራዎች ልዩ ጥንቃቄ ያስፈልጋል ብለዋል።

እንደ አቶ ንጉሱ ገለፃ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የተለያዩ የመንግስት አካላት ጥረት እንዳለ ቢሆንም የህብረተሰቡ ትብብርና ጥረት ካልታከለ ውጤት አይኖረውም።

በመሆኑም የኮሮናቫይረስ መስፋፋትን ለመግታት በጋራ በመቆም፣ በመተባበርና በመረዳዳት ይህንን አስቸጋሪ ወቅት ማለፍ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም