“ሕወሓት የተሻለ ሀሳብ ያለውን አመራር የሚያስተናግድበት ሜዳ የለውም”… የሕወሓት ከፍተኛ አመራር የነበሩ

786

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18/2012 (ኢዜአ) “ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) የተሻለ ሀሳብ ያለውን አመራር የሚያስተናግድበት ሜዳ የለውም” ሲሉ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራር የነበሩት አቶ ሚሊዮን አብርሃ ተናገሩ።

“የትግራይ ወጣት ከአንድ አቅጣጫ ብቻ የሚመጣን አስተሳሰብ በመቀበል ጦርነት ናፋቂ ሊሆን አይገባም” ብለዋል።

የሕወሓት ከፍተኛ አመራር የነበሩት አቶ ሚሊዮን አብርሃ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ”ሕወሓት የተሻለ ሀሳብ ይዞ የሚመጣን አመራር ወደኋላ የማስቀረት አባዜው የጀመረው ዛሬ አይደለም” ብለዋል።

በዚህም ክልሉን ብሎም አገርን መለወጥ የሚችሉና በትግሉ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ የነበራቸው ወጣቶች ከድርጅቱ እየተንጠባጠቡ መውጣታቸውን ነው ያነሱት።

አቶ ሚሊዮን ከድርጅቱ እንዲለቁ ካስገደዷቸው ምክንያቶች ዋነኛው ድርጅቱ ለሀሳብ ልዩነት ቦታ  አለመስጠቱና ዘመኑ ከሚፈልገው ለውጥ ጋር ለመሄድ ፍላጎት ያለመኖር መሆኑን አንስተዋል።

እንደ አቶ ሚሊዮን ገለጻ፣ በየትኛውም የፖለቲካ ርዕዮተ-ዓለም ተመሣሣይ አስተሳሰብ የማራመድ ግዴታ አይጣልም።

ልዩነቶችን በሰላማዊና በአሳማኝ ሁኔታ መፍታት በሀሳብ መሸናነፍ የሚቻልበትን የፖለቲካ ምህዳር አጥብቧል ብለዋል።

ከዚህ ባለፈ በድርጅቱ ልዩነቶችን እስከመጨረሻው ይዞ መቆየት እንደ ነውር የሚቆጠርበት ሁኔታ መፈጠሩን ነው ያነሱት።

እንደ አቶ ሚሊዮን ገለጻ በሕወሓት ሥም እየተንቀሳቀሱ ያሉ ጥቂት ቡድኖች የትግራይ ሕዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር በነፃነትና በትብብር እንዳይሰራ እያደረጉ ነው።

የክልሉን ሕዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ከመፍታት ይልቅ የብሽሽቅ ፖለቲካን በማራመድ ሕዝቡ ሌሎች ወንድሞቹን እንዲጠላ እያደረጉ ነው።

የትግራይ ሕዝብ ከመላ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር በፍቅርና በሰላም መኖሩን ጠቅሰው በአሁኑ ጊዜ ግን አብዛኛው ሕዝብ ጥቂት የሕወሓት ቡድኖች በሚፈጥሩት ፕሮፓጋንዳ ጥርጣሬ ውስጥ እንዲገባ አድርጓል ይላሉ።

በዚህም ወጣቱ ከልማት ይልቅ ለጦርነት ልቡን በማነሳሳት ወደ ጥፋት የሚገፋፋ ነው ብለዋል።

”ሃይማኖትና ሕዝብ አንድ አይደለም፤ ፖለቲካና ሕዝብም አንድ አይሆኑም” ያሉት አቶ ሚሊዮን ሕወሓትና የትግራይ ሕዝብ የተለያዩ መሆናቸውን አጽንኦት ሊሰጠው ይገባል ነው ያሉት።

ሕወሓት በሀሳብ ልዩነት ሳይሆን በንትርክና በሹኩቻ በመምራት የትግራይን ሕዝብ ከልማትና ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ወደኋላ ያስቀረ ድርጅት መሆኑንም ነው የገለጹት።

”ሕወሓት አገር በሚያስተዳድርበት ጊዜም የትግራይ ሕዝብ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ የሆነለት አልነበረም” ያሉት የቀድሞ የሕወሓት ከፍተኛ አመራር በዚህም እንደ ሌሎች ሕዝቦች ለውጡን ይፈልገው እንደነበር አስታውሰዋል።

ለውጥ ፈላጊው የትግራይ ሕዝብ  ከኢትዮጵያዊያን ወንድሞቹ እገዛ ከተደረገለት ሕወሓትን ወደ ትክክለኛ መስመር መመለስ ካልሆነም ማክሰም ይችላል ብለዋል።

ብልጽግና ፓርቲ ለትግራይ ሕዝብ በተለይ ለወጣቱ የሥራ ዕድልን በማመቻቸትና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ጥሩ ዕድል ይዞ መምጣቱንም ነው ያብራሩት።

የትግራይ ሕዝብ በተለይ ወጣቱ ከአንድ አቅጣጫ ብቻ የሚመጣን አስተሳሰብ በመቀበል ከሰላምና ልማት ይልቅ ጦርነት ናፋቂ እንዳይሆንም ጥሪ አቅርበዋል።


አቶ ሚሊዮን በሕወሓት ውስጥ በነበሩበት ጊዜ ከሰሩባቸው የሥራ ኃላፊነቶች መካከል በቀድሞው የኢህአዴግ ጽሕፈት ቤት የገጠር ፖለቲካ ዘርፍ የቢሮ ኃላፊ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የኢህአዴግ ተወካይ፣ እንዲሁም በድርጅቱ የፖለቲካ ርዕዮተ-ዓለም ቢሮ ኃላፊ ይጠቀሳል።