የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በአርሲ ዞን ሄጦሳ ወረዳ የስንዴ መካናይዜሽን ክላስተር ጎበኙ

218

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18/2012 (ኢዜአ) የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ሄጦሳ ወረዳ ለስንዴ ምርት ዝግጁ የተደረገውን መካናይዜሽን ክላስተር ጎበኙ።

የፓርቲው አመራር አባላት የጎበኙት ለስንዴ ምርት ዝግጁ የተደረገውን 80 ሄክታር ሜካናይዜሽን ክላስተር ነው።

መሬቱን በዘር ለመሸፈን ዝግጁ የተደረገ ሲሆን በዚሁ የምርት ክላስተር ማእቀፍ 65 የአካባቢው አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ሆነዋል።

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ዳባ ደበሌ እንደገለጹት አሰራሩ ምርትን ለመጨመርና አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል ነው።

የክላስተር አመራረት ሂደት ሁሉንም አርሶ አደሮች በፍትሃዊነት ተጠቃሚ የሚያደርግ አሰራር መሆኑንም አብራርተዋል።

በአሁኑ ወቅት በክልሉ ከ2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በክላስተር በመልማት ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢፌዲሪ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዛዲግ አብርሃ በበኩላቸው በክልሉ የተጀመሩ ስራዎች የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መሆናቸውን መመልከታቸውን ገልጸዋል።

እየተከናወኑ ያሉ የግብርና ስራዎች ኢትዮጵያ ወደ ኢንዱስትሪ መር ልማት ለመሸጋገር ለምታደርገው ጥረት አጋዥ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

የብልፅግና ፓርቲም ለዚሁ ስኬት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የብልፅግና ፓርቲ አስተዳደር ዘርፍ ሃላፊ አምባሳደር ሃሰን አብዱልቃድር እንዳሉትም በኦሮሚያ ክልል እየተከናወኑ ያሉ የግብርና ስራዎች ተስፋ ሰጭዎች ናቸው።

በተለይም በክላስተር የማምረት ሂደቱ በተጠናከረ መልኩ እየተሰራበት መሆኑን በጉብኝቱ አረጋግጠናል ብለዋል።

በጉብኝቱ የብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብናልፍ አንዷለም፣ የኦሮሚያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማን ጨምሮ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ሌሎች የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም