ኢንዱስትሪ ፓርኮች በኮቪድ-19 ምክንያት የሚደርስባቸውን ጫና ለመቀነስ ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው

63

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18/2012 (ኢዜአ) ኢንዱስትሪ ፓርኮች በኮቪድ-19 ምክንያት የሚደርስባቸውን ጫና ለመቀነስ መንግስት የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑ ተገለጸ። ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከፓርኮቹ 122 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል።

ኢትዮጵያ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የምታደርገውን ሽግግር ለማፋጠን በተለያዩ ክልሎች ኢንዱስትሪ ፓርኮች ተገንብተው ወደ ሥራ ገብተዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራአስፈጻሚ ወይዘሮ ለሊሴ ነሜ ለኢዜአ እንዳሉት የኮቪድ -19 ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ መከሰቱን ተከትሎ በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ምርቶች ላይ የገበያ መቀዛቀዝ ታይቷል።

የገበያ መቀዛቀዙ እንዲያንሰራራ ለማድረግና ባለሃብቱን ለማበረታታት መንግስት የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል።

ከድጋፎቹ ውስጥ ምርቶቻቸውን ወደ ውጪ መላክ ያልቻሉ ባለሃብቶች በአገር ውስጥ ገበያ ምርቶቻቸውን ለሁለት ወራት እንዲሸጡ ማድረግ አንዱ ነው።

ከዚህ ባለፈ ባለሃብቶች ለረጅም ጊዜ ሲያነሱት የነበረው የትራንስፖርትና የማጓጓዣ አገልግሎት ክፍያ ላይ ቅናሽ መደረጉንም ነው ሥራ አስፈጻሚዋ የተናገሩት።

እንደ ወይዘሮ ለሊሴ ገለጻ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ቢከሰትም ትዕዛዛቸው ያልተቋረጠ ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን ወደ ውጪ መላከ አላቋረጡም።

''ምርቶቻቸውን መላክ ያልቻሉ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ድርጅቶችም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ምርቶችን በማምረት ላይ ናቸው'' ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ተመርተው ወደ ውጪ ከተላኩት የተገኘው ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ብልጫ እንዳለው ወይዘሮ ለሊሴ ገልጸዋል።

ለዚህ በአገሪቷ የሰፈነው ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም የሠራተኞች የማምረት አቅምና ከባለሀብቶች ጋር ተናቦ የመስራት ባህል ማደግ ምክንያት መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በመንግስት ተገንብተው ወደ ሥራ ከገቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ሃዋሳ፣ ቦሌ ለሚ ቁጥር አንድ አይሲቲ፣ መቐለ፣ ኮምቦልቻ፣ አዳማ፣ ጅማና ደብረ ብርሃን፣ ድሬዳዋ፣ ባህር ዳር፣ ተጠቃሽ ናቸው።

በፓርኮቹ እስካሁን ከ70 ሺህ በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል ያገኙ ሲሆን ፓርኮቹ በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ ሲገቡ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም