በአፍሪካ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ 1 መቶ ሺህ አለፈ

120

ግንቦት 18/2012(ኢዜአ) በአፍሪካ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ከ1 መቶ 12 ሺህ በላይ መድረሱን ሲዲሲ አፍሪካ አስታውቋል።

የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ተቋም ዛሬ እንዳስታወቀው ባለፉት አራት ቀናት ብቻ 19 ሺህ 942 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሲሆን፤ 8 ሺህ 803 የሚሆኑት ደግሞ አገግመዋል።

447 የሚሆኑት ደግሞ በአራት ቀናት ውስጥ በቫይረሱ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

በአጠቃላይ በአፍሪካ 112 ሺሕ 290 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ፤ 44 ሺህ 920 ሰዎች አገግመው 3 ሺህ 359 ህይወታቸውን አጥተዋል።

ተቋሙ እንዳመለከተው፤ 14 ሀገራት በሚገኙበት ምሰራቅ አፍሪካ ባለፉት 4 ቀናት 2 ሺህ 594 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል፤ 58 ሰዎችም ሕይወታቸውን አጥተዋል ሌሎች 325ቱ ደግሞ አገግመዋል።

በቫይረሱ ከተጠቁ 14 ሀገራት በሚገኙበት በዚሁ የአህጉሪቱ ክፍል በአጠቀላይ 12 ሺህ 291 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ፣ 332 ሞተዋል፤ 3 ሺህ 295 ሰዎች ደግሞ አገግመዋል።

በተቃራኒው ዘጠኝ ሀገራት በቫይረሱ በተጠቁበት መካከለኛው አፍሪካ ባለፉት 4 ቀናት 2 ሺህ 742 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል፤ 41 ሰዎችም ሕይወታቸውን አጥተዋል ሌሎች 124ቱ ደግሞ አገግመዋል።

በመካከለኛው አፍሪካ 11 ሺህ 906 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ፤340 ሰዎች ሲሞቱ 3 ሺህ 94ቱ አገግመዋል።

በቫይረሱ ክፉኛ በተጠቃው የሰሜን አፍሪካ ክፍል ባለፉት 4 ቀናት ውስጥ 5 ሺህ 277 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ፤ 153 ሰዎች በዚሁ ቫይረስ ሳቢያ ሕይወታቸውን አጥተው 2 ሺህ 702ቱ ደግሞ አገግመዋል።

በሰሜን አፍሪካ ከሚገኙት ስድስት ሀገራት 34 ሺህ 429 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ፤ ከዚህ ውስጥ 1 ሺህ 621 ሕይወታቸውን ሲያጡ ፣ 15 ሺህ 94 ሰዎች አገግመዋል።

ሰሜን አፍሪካ በአፍሪካ በቫይረሱ በተያዙ ሰዎች ቁጥር ቀዳሚ ዞን ነው።

በኮቪድ 19 በተጠቁ ሰዎች ቁጥር ሰሜን አፍሪካን ተከትላ የምትገኘው ምዕራብ አፍሪካ ባለፉት አራት ቀናት ውስጥ 3ሺሕ 705 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ፤ 75 ሰዎች ለሕልፈት ተዳርገዋል።

1 ሺሕ 838 ደግሞ በአራት ቀናት ውስጥ አገግመዋል።

በምዕራብ አፍሪካ 29 ሺህ 433 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ፤ ከዚህ ውስጥ 11 ሺህ 686 ሰዎች አገግመው፣ 615ዎቹ ሞተዋል።

በዓመቱ መጨረሻ 40 ሺህ ዜጎቿን በቮይረሱ ምክንያት በሞት ትነጠቃለች የተባለችው ደቡብ አፍሪካ የምትገኝበት ደቡባዊው የአአፍሪካ ክፍል ባለፉት አራት ቀናት ውስጥ 5 ሺህ 624 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ፤ 124 ሰዎች ሞተው፣ 3 ሺህ366ቱ አገግመዋል።

በዚህ የአህጉሪቱ ክፍል 24 ሺሕ 231 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ፤ 11ሺህ 751 አገግመው፣ 451ዱ ሞተዋል።

በዓለም ላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ5 ነጥብ 5 በላይ መድረሱን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም