ከፋይናንስ ተቋማት ውጭ የሚንቀሳቀሰውን ጥሬ ገንዘብ ወደባንክ ሥርዓት ለመመለስ የብር ኖቶችን መቀየር ይገባለ ተባለ

152

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ከመደበኛ የፋይናንስ ተቋማት ውጭ የሚንቀሳቀሰውን ጥሬ ገንዘብ ወደ ባንክ ሥርዓት ለመመለስ የብር ኖቶችን መቀየር እንደሚገባ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ገለጹ።

መንግሥት ከባንኮች በሚወጣው ጥሬ ገንዘብ ላይ ያስቀመጠውን ገደብ ተፈጻሚ ለማድረግ የቼክ ክፍያ ሥርዓቱን ማዘመን አለበትም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር በቀረበለት ጥናት መሠረት ግለሰቦች በቀን 200 ሺህ፣ በወር አንድ ሚሊዮን ብር፤ ተቋማት ደግሞ በቀን 300 ሺህ፣ በወር 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ብቻ እንዲያወጡ የሚያስገድድ መመሪያ በቅርቡ ማውጣቱ ይታወቃል።

መመሪያው ተግባራዊ የተደረገውም የባንኮች ተቀማጭ የጥሬ ገንዘብ መጠን ስለተመናመነ ሳይሆን ከባንኮች ውጭ ያለው ገንዘብ በመደበኛ የፋይናንስ ተቋማት በማዘዋወር ወንጀልን ለመከላከል ብሎም ወደ ዘመናዊ የባንክ ሥርዓት ለመግባት እንደሆነ ተደጋግሞ ተነግሯል።

ጉዳዩ በአንድ በኩል "በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት እየጨመረ የመጣውን የጥሬ ገንዘብ ፍላጎት ግምት ውስጥ አላስገባም" በሌላ በኩል "ወንጀልን ለመከላከልና የግብር ስወራን ለማስቆም ሁነኛ መፍትሔ ነው" በሚል በሁለት ጎራ ክርክር አስነስቷል።

በኢትዮጵያ ስቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር አቶ መዚድ ናሲር ለኢዜአ እንዳሉት በጥሬ ገንዘብ አጠቃቀም ላይ የተጣለው ገደብ ከወንጀል መከላከል ባሻገር ባንኮች ተቀማጭ የጥሬ ገንዘብ እጥረት ያጋጠማቸው ይመስላል።

"መንግሥት እንዳለው ባንኮችም ወንጀሉ አሳስቧቸው ያወጡት መመሪያ ከሆነ በጥሬ ገንዘብ ላይ የተጣለው ገደብ ውጤታማ እንዲሆን የብር ኖቱን መቀየር ይገባል" ብለዋል።

የጥሬ ገንዘብ እጥረቱ የተከሰተው በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት መሆኑን የገለጹት አቶ መዚድ፤ መመሪያው የተከሰተውን የኢኮኖሚ ጫና ለመቀነስ ያግዛል ተብሎ የታሰበ እንደሆነ ነው የሚናገሩት።

የልማት ኢኮኖሚክስ ባለሙያው አቶ ደረጀ ደጀኔ በበኩላቸው "በገጠሪቱ አካባቢ በኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ ተቋማትና ግለሰቦች ለቀን ሠራተኞቻቸው ጥሬ ገንዘብ ስለሚከፍሉ እጥረት ሊገጥማቸው ይችላል" ብለዋል።

ነገር ግን በፊትም ተቋማት ከአምስት ሺህ ብር ጀምሮ መክፈል የሚችሉት በቼክ ስለሆነ መመሪያው ወደ ሕጋዊነት እንዲመጡ የሚያግዝ እንጂ ጉዳት እንደሌለው ያስረዳሉ።

አቶ ደረጀ እንደሚሉት መመሪያው ግቡን እንዲመታ ባንኮች የሚከተሉትን የቼክ ገንዘብ ግብይት ሥርዓት ዘመናዊ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

በኢትዮጵያ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርና ታክስ ስወራ የጀግንነት መገለጫ እስኪመስል ድረስ ከልክ በላይ እንዳለፈ ነው የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የተናገሩት።

በመሆኑም መንግሥት የግብር ማጭበርበርና ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመከላከል የጥሬ ገንዘብ ገደብ ከማስቀመጥ ባለፈ የታክስ ሥርዓቱን ማስተካከል እንዳለበት ይመክራሉ አቶ መዚድ።

በዓለም የጤና ድርጅት ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ የሆነው ኮቪድ-19 ከጤና አልፎ በኢኮኖሚው ላይ ያሳደረው አሉታዊ ተፅዕኖ ሚሊዮኖችን ለረሀብ ይዳርጋቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም