አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሁሉም ካምፓሶች የፊት ጭንብል መልበስ ግዴታ መሆኑን አስታወቀ

94

ግንቦት 17/2012 (ኢዜአ) በአገሪቱ የሚታየው የኮሮናቫይረስ ስርጭት ከዕለት ወደ ዕለት እያደገ በመምጣት በአሁኑ ወቅት አሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የገለጸው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከግንቦት 17 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም ካምፓሶቹ የፊት ጭንብል ማድረግን አስገዳጅ የሚያደርግ መመሪያ አውጥቷል።

ዩኒቨርሲቲው የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ቀደም ሲል ያስተላለፋቸው መሠረታዊ የመከላከል ዘዴዎች የሆኑት እጅ መታጠብ፣ ርቀት መጠበቅ እና የፊት ጭንብል መጠቀም በመላው የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ዘንድ ተግባራዊ እንዲሆን በማድረግ የሚያበረታታ እንቅስቃሴ ሲያደርግ መቆዩቱን አስታውሷል።

ነገር ግን የተላለፉት የጥንቃቄ እርምጃ መመሪዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ መላላት እየታየባቸው በመሆኑ እና የቫይረሱ ስርጭት እየተጠናከረ መምጣቱን ጠቅሷል።

ይህንን ተከትሎ ከግንቦት 17 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ማንኛውም ሰው የፊት ጭንብል ሳያደርግ ወደ ግቢ መግባት፣ በግቢ ውስጥ ያለ ጭንብል መንቀሳቀስ እና ጭንብል ሳያደርጉ በቢሮ ውስጥ ሥራ መሥራት በጥብቅ የተከለከለ መሆኑን አስታውቋል።

የዩኒቨርሲቲው ስታንዳርድስ ሴፍቲ እና ሴኪዩሪቲ ዳይሬክተር እና የሚመለከታቸው የሥራ ክፍል ሐላፊዎች መመሪያውን ተግባራዊ እንዲያደርጉም አሳስቧል ሲል የዘገበዉ ኢብኮ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም