በአዳማ ከተማ የተሽከርካሪ አደጋ የሰዎችን ህይወት አጠፋ

77

አዳማ (ኢዜአ ) ግንቦት 17/2012   በአዳማ ከተማ ዛሬ በደረሰው የተሽከርካሪ አደጋ የሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ። 

የከተማዋ ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ረዳት ኢንስፔክተር ወርቅነሽ ጋልሜቻ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት አደጋው የደረሰው በአዳማ ቦኩ ክፍለ ከተማ በሬቻ ቀበሌ ውስጥ ነው።

ጠዋት አስራ ሁለት ሰዓት ተኩል አካባቢ የታርጋ ቁጥሩ ኮድ 3-67804 አ.አ  የጭነት አይሱዙ ከኮድ 1- 54323 ኦ.ሮ  ባጃጅ ጋር በመጋጨቱ የአንድ እናት ህይወት አልፏል።

በተጨማሪም በአንድ ሰው ላይ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶ በአዳማ ሪፌራል ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገለት ነው።

በተመሳሳይም የታርጋ ቁጥሩ  ኮድ 1-30419 ኦሮ  የህዝብ ማመላለሻ ታክሲ በመንገድ ዳር ቆማ የነበረችውን ወጣት በመግጨት ህይወቷ እንዲያልፍ  ምክንያት መሆኑን  ረዳት ኢንስፔክተር ወርቅነሽ ተናግረዋል።

የአደጋው መንስኤ የጥንቃቄ ጉድለት እንደሆነ ጠቁመው አሽከርካሪዎቹ በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም  አመልክተዋል።