አፍሪካዊያን ለኮቪድ-19 ፈንድ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉ ተጠየቀ

67

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 17/2012 ዓ.ም ( ኢዜአ) የአፍሪካ ኅብረት ለኮሮናቫይረስ /ኮቪድ-19/ ምላሽ ላቋቋመው ፈንድ አፍሪካዊያን የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቀረበ።

የኮቪድ-19 ምላሽ ፈንድ በኅብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት መጋቢት 17 ቀን 2012 ዓ.ም መቋቋሙ ይታወቃል።

ፈንዱ በአፍሪካ ያለውን የኮሮናቫይረስ ምላሽ አቅም ማጠናከርና ቫይረሱ በዜጎች ላይ የሚያስከትለውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ መቋቋም የሚያስችሉ ስራዎችን መደገፍ ዓላማው ነው።

የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የዛሬው የአፍሪካ ኅብረት የተቋቋመበትን ዕለት በማስመልከት የአፍሪካ ቀን ለ57ኛ ጊዜ ዛሬ እየተከበረ ይገኛል።

ኅብረቱ ለአፍሪካዊያን፣ ትውልደ አፍሪካዊያንና ለአገራቱ በ'አፍሪካ ቀን' ለኮቪድ-19 ምላሽ ፈንድ "ትንሽ ስጡ" የሚል ጥሪ አቅርቧል።

በፈንዱ በሚሰበሰበው ገንዘብ በምን ተግባራት ላይ እንደሚውልም በድረ ገጹ አስፍሯል።

የመጀመሪያው ፈንዱ በኮሮናቫይረስ ምክንያት በአፍሪካ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ ለመቋቋም ለሚሰሩ ስራዎች እንደሚውል ገልጿል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ አፍሪካ ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት በማህበራዊና ኢኮኖሚ መስኮች ያገኘቻቸውን ለውጦች የመቀልበስ አደጋ መደቀኑን ነው ኅብረቱ የገለጸው።

ወረርሽኙ በአፍሪካ ዜጎች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታ ላይ ከባድ ተጽዕኖ የማሳደር አቅም አለውም ብሏል።

የአፍሪካ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል ለኮቪድ-19 እና ሌሎች ድንገተኛ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች የሚሰጠውን ምላሽና አቅም ማጠናከር የፈንዱ ገንዘብ የሚውልበት ሁለተኛው ተግባር ነው።

የአፍሪካ ኅብረት ማዕከሉ እ.አ.አ በ2014 በምዕራብ አፍሪካ ተከስቶ ከነበረው የኢቦላ ቫይረስ በኋላ መመስረቱን ያወሳል።

በወቅቱ የኢቦላ ቫይረስ በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ህይወት እንዲያልፍ ምክንያት መሆኑንና የዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ኑሮ ላይም ከባድ ጉዳት አድርሶ ማለፉን ገልጿል።

ማዕከሉ በተቋቋመበት ደንብ ላይ በተሰጠው ዋኘኛ ተልዕኮ መሰረት በአፍሪካ ጠንካራ የኅብረተሰብ ጤና ተቋም ሚናውን ለመወጣት የሚያስችለውን ተግባር እንዲከውን ከፈንዱ ላይ ድጋፍ እንደሚደረግለት ተመልክቷል።

ለኮቪድ-19 የሚያስፈልጉ የሕክምና መሳሪያዎችና ቁሳቁሶች ግዥና ስርጭት እንዲሁም የኅብረቱ አባል አገራት ለወረርሽኙ የሚሰጡትን ፈጣን ምላሽ ማጎልበት ሌላው የፈንዱ ገንዘብ የሚውልበት ስራ ነው።

የኮቪድ-19 የህክምና መሳሪያዎችና ቁሳቁሶች ለመግዛት በዓለም ገበያ ጠንካራ ፉክክር እንዳለ የአፍሪካ ኅብረት ገልጿል።

የሕክምና እቃዎችና መሳሪያዎች በኅብረቱ ተገዝተው በማዕከሉ በኩል ለአባል አገራት እንዲሰራጩ እየተከናወነ ያለው ስራ በፈንዱ አማካኝነት ድጋፍ ይደረግለታል።

በተጨማሪም በኮቪድ-19 ከተያዙ ሰዎች ጋር ንክኪ ያላቸውን ሰዎች ለማገዝ ለሚሰማሩ አንድ ሚሊዮን የማኅበረሰብ ጤና ሰራተኞችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በፈንዱ እንደሚደገፉ ህብረቱ አስታውቋል።

የአፍሪካ ኅብረት ኮቪድ-19 ምላሽ ፈንድ በዳይሬክተሮች ቦርድ የሚመራ ሲሆን ቦርዱ ከአፍሪካ መንግስታት ስምንት፣ ከግሉ ዘርፍ የተውጣጡ ሁለት በድምሩ 10 አባላት አሉት።

የአፍሪካ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጆን ንኬንጋሶንግ የኮቪድ-19 ምላሽ ፈንድ ዋና ጸሐፊ ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ የአፍሪካ ቀንን አስመልክቶ በፌስቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት በብዙ ጸጋ የታደለችው ሁሉም ዓይነት ብዝኃነት የሞላባት አፍሪካ መድረሻዋ መልከ ብዙ ብልጽግና እንደሆነ ገልጸዋል።

'ዛሬ የአፍሪካን ቀን ስናከብር የምንፈልጋትን አፍሪካ እውን ለማድረግ አንድነታችንን እናጠንክር' ብለዋል።

የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት እ.አ.አ በ1963 አዲስ አበባ ላይ በ32 የአፍሪካ አገራት ነው የተመሰረተው።

እ.አ.አ በ1999 በሊቢያ ሲርጥ ከተማ በተካሄደው ስብሰባም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ቀርቶ የአፍሪካ ኅብረት ተመሰርቷል።

የአፍሪካ ኅብረት 55 አባል አገራት አሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም