በሦስት ክልሎች የተጠናከረ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ መከናወኑ ተገለፀ

119
አዳማ ግንቦት1/2010 ዘንድሮ በህብረተሰቡ ተሳትፎ የተጠናከረ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራ መከናወኑን የኦሮሚያ፣ አማራና ጋምቤላ ክልሎች አስታወቁ። የፌዴራልና የክልሎች የ2010 የተፈጥሮ ሃብት ልማት የጋራ የምክክር መድረክ በቢሾፍቱ ከተማ ተካሄዷል፡፡ በመድረኩ ላይ የተሳተፉት የኦሮሚያ ክልል የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ተወካይ አቶ ስለሺ ለማ በተለይ ለኢዜአ እንዳስታወቁት ዘንድሮ የክልሉን ህዝብ በማሳተፍ የተጠናከረ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ ተካሄዷል። በልማት ስራው በክልሉ በ3 ሺህ 837 አዳዲስ ተፋሰሶች የሚገኝ 1 ሚሊዮን 384 ሺህ ሄክታር መሬት ማልማት መቻሉን ጠቅሰዋል። በዚሁ የተፋሰስ ልማትም ከ861 ኪሎ ሜትር የአፈርና የድንጋይ እርከን እንዲሁም ከ572 ኪሎ ሜትር በላይ የማሳ ላይ እርከን በህብረተሰቡ ነፃ የጉልበት ተሳትፎ ተሰርቷል። በተጨማሪም 596 ሺህ ሜትር ኪዩብ የጋቢዮንና ድንጋይ ክትር፣ 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሜትር ኩብ የጎርፍ ማስወገጃ ቦይ፤ የተራራና ጠረዼዛ እርከንም መሰራቱን ጠቁመዋል። ከዚህ ጎን ለጎንም የተጎሳቆለ 435 ሺህ ሄክታር መሬት ተከልሎ ከሰውና እንስሳት ንክኪ እንዲጠበቅ የተደረገ ሲሆን በርካታ እርጥበት ማቆያ እስትራክቸሮች መሰራታቸውን ተናግረዋል፡፡ እንደ ተወካዩ ገለፃ በኦሮሚያ ባለፉት ስድስት ዓመታት ከ3 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በአፈርና ውሃ ጥበቃና ልማት ስራ ለምቷል፤ የተራቆተ የግልና የማህበረሰብ መሬትም አገግሞ ወደ ምርት ገብቷል። የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ተወካይ አቶ አብዮት በላይ በበኩላቸው በዚህ ዓመት በክልሉ በ6 ነጥብ 8 ሚሊዮን የተደራጀ ህዝብ የተሳተፈበት የተፋሰስ ልማት ስራ ተከናውኗል፡፡ በክልሉ 154 ወረዳዎች በተደረገው እንቅስቃሴ በ292 ሺህ 343 ሄክታር ማሳ ላይ የእርከን ስራን ጨምሮ በርካታ የእርጥበት ማስረጊያ ስትራክቸሮችና የተራራ ልማት ተካሄዷል። 1 ሺህ 458 የእጅ ውሀ ጉድጓድና የማህበረሰብ ኩሬ ቁፋሮ የተከናወነ ሲሆን በ17 ሺህ 840 ሄክታር መሬት ላይ የተከሰተውን መጤ አረም የማስወገድና የመከላከል ስራም ተከናውኗል፡፡ የጋምቤላ ክልል የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ተወካይ  አቶ ካሣሁን ሞላ በበኩላቸው በክልሉ በሶስት ዞኖችና 13 ወረዳዎች በዚህ ዓመት ብቻ በ2 ሺህ 232 ተፋሰሶች ላይ የአፈርና ውሃ እቀባ ስራ ተሰርቷል፡፡ እንዲሁም 900 ሄክታር የተጎሳቆለና ከጥቅም ውጪ የሆነ መሬት በመከለል ከሰውና እንስሳት ንክኪ ነፃ ሆኖ እንዲያገግም በመደረግ ላይ ነው፡፡ ለተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና እንክብካቤ ስራው ከ32 ሺህ በላይ ነዋሪዎች መሳተፋቸውን ገልጸው ለስራው አጋዥ የሆኑ ከ10 ሺህ በላይ የተለያዩ የእጅ መሳሪያዎች ተሰራጭተዋል። ባለፉት ጊዜያት የተከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራዎችን በእውቀትና በክህሎት ያለመምራት የተሰሩትንም በመንከባከብ  እንዲሁም አርሶ አደሩ ሥራውን  በባለቤትነት በመጠበቅና በመንከባከብ ረገድ ክፍተቶች እንደነበሩ የየክልሎቹ ተወካዮች ጠቅሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም