የህገ መንግስት ትርጉም ጥያቄና የአሰራር ሂደቶች

1599

በዳግም መርሻ/ከኢዜአ/

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ባሳረፈው ዳፋ ምክንያት የበርካታ የአለም ሀገራት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይወት ተመሰቃቅሏል። በኢትዮጵያም ያለው ሁኔታ ከዚህ የተለየ አይደለም። ወረርሽኙ ተጽእኖ ካሳረፈባቸው ፖለቲካዊ ጉዳች አንዱ በብዙዎች ዘንድ ትልቅ ግምት ተሰጥቶትና ቀን ተቆርጦለት የነበረው የ2012 ዓ.ም ምርጫ ነው።

ከዚህ ጋር ተያይዞ በበሽታው ምክንያት ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ይካሄዳል ተብሎ የታቀደው 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ማካሄድ እንደማይችል ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ማስታወቁ ይታወሳል። ይህን ተከትሎ አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የመምራት ጊዜው የፊታችን መስከረም ወር ላይ ሲያበቃ ቀጣይ ሀገር የመምራት ሀላፊነት በምን መልኩ ሊቀጥል ይገባል ለሚለው ጥያቄ ከቀረቡት አራት የመፍትሄ አማራጮች መካከል የህገ መንግስት ትርጓሜ መስጠት የሚለው ሀሳብ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአብላጫ ድምጽ በማጽደቅ ለህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ መርቶታል። በምክር ቤቱ ትርጉም እንዲሰጥባቸው የቀረቡት ጭብጦች፦

  • በኢትዮጵያ የቅድመ ምርጫ ዝግጅቶች እና ምርጫ በሚደረግበት ወቅት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ የሚያስገድድ ሁኔታ ቢከሰት፣ በዚህም የተነሳ ምርጫ ማድረግ የማይቻል ቢሆን የምርጫ ዘመናቸው ያበቃው ምክር ቤቶች እና የአስፈፃሚው አካል የስራ ዘመን ምን ይሆናል?
  • የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲታወጅ ምክንያት የሆነው ክስተት ከተወገደ በኋላ ምርጫውስ በምን ያክል ጊዜ ውስጥ ሊከናወን ይገባል? የሚሉ የትርጉም ጥያቄዎች ናቸው።

ለመሆኑ አሁን ላይ የብዙዎችን ቀልብና ትኩረት የሳበው የህገ መንግስት ትርጉም ምን ማለት ነው? ስለ ህገመንግስት ትርጉም ምንነት ትክክለኛ የሆነ ግንዛቤ ለመያዝ በመጀመሪያ ስለ ህገ መንግስት ትርጓሜ እና ይዘት ማወቅ ጠቃሚ ነዉ፡፡

ህገ መንግስት በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የፖለቲከኞች፣ የህግ ባለሙያዎችና የዜጎች መነጋገሪያ አጀንዳ እየሆነ የመጣ ፖለቲካዊ ጽንሰ ሀሳብ ነው።  ከዚህ ጋር በተያያዘ ሰዎች ስለራሳቸው ሀገር ወይም ስለሌሎች ሀገራት  ህገ መንግስት አንስተዉ ሲናገሩና ሲከራከሩ ይሰማል፡፡ ሰዎች ስላላቸው መብትና ግዴታቸው ሲናገሩ፣ ስለ ምርጫ ሂደትና አፈጸጸም ሲወያዩ፣ በፍርድ ቤትና በተለያዩ ቦታዎች ጉዳያቸዉን አቅርበዉ ሲከራከሩ፣ ሲያስረዱ እና ከፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ጋር አያይዘው ሲነጋገሩ ህገ መንግስት የሚለዉን ቃል ሀሳባቸውን ለማጠናከር ሲጠቀሙበት ይስተዋላል፡፡ ይህ የሚያሳየው ህገ መንግስት በብዙኃኑ ዘንድ እውቅና እያገኘ የመጣ ሰነድ መሆኑን ነዉ፡፡

ህገ መንግስት በፅንሰ ሀሳብ ደረጃ ከዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ ከመልካም አስተዳደር፣ ከምጣኔ ሀብት እድገት ወይም ማሽቆልቆል፣ ከሰብዓዊ መብቶች አያያዝና ጥበቃ ጋር በጥብቅ ይቆራኛል፡፡ ነገር ግን ብዙ ሰዎች ህገ መንግስት የሚለዉን ቃል አዘውትረው የሚጠቀሙ ቢሆንም ሁሉም ሰዎች ሰለ ህገ መንግስት ምንነት በትክክል ያዉቃሉ  ወይም ደግሞ ትክክለኛ ግንዛቤ ቢኖራቸውም ድንጋጌዎቹን ይተገብራሉ ተብሎ አይገመትም፡፡

ይልቁንም ህገ መንግስቱን  በተሳሳተ(በተጣመመ) መልኩ አልያም የራሳቸውን ጥቅምና ፍላጎት እንዲያሟላ ከመሻት አንጻር  የሚተረጉሙትና የሚረዱት ሰዎች እንዳሉ መገንዘብ ይቻላል፡፡  አምባገነን መንግስታትም በህገ መንግስት እየማሉና እየተገዘቱ ኢ-ህገ መንግስታዊ ተግባራትን ሲፈጽሙ የሚስተዋሉበት ሁኔታ ጥቂት የሚባል አይደለም።

ህገ መንግስት የህጎች ሁሉ የበላይ ህግ እና መንግስት በምን አይነት መንገድ እንደሚመሰረት፣ እንደሚመራና እንደሚተዳደር፣ የስልጣን ምንጭ ክፍፍልና የቁጥጥር ሂደትን የሚያመላክት፣ የዜጎችን ጥቅል መብትና ግዴታ የሚተነትን፣ የመንግስት አካላት አደረጃጀት፣ ሀላፊነትና ተግባር የሚያስቀምጥ፣ የሀግ አውጪ፣ አስፈጻሚና ተርጓሚ አካላት የሚመሩበትን መርህ የሚያስቀምጥ፣ የመንግስት ቅርጽ ስልጣንና የስልጣን ወሰን የሚዘረዝር፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና  ኢኮኖሚዊ ጉዳዮችን የሚዳስስ፣ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የሚነካና ጥቅል አቅጣጫ የሚያመላከት ነው።

በአጠቃላይ ህገ መንግስት በዋነኛነት አንዲት አገር ወይም አንድ መንግስት የሚተዳደርባቸዉ መሰረታዊ መርሆችን እና ደንቦችን የሚይዝ የህግ ማዕቀፍ ነዉ፡፡

በሌላ በኩል ህገ መንግስት የአንድ ሀገር ህብረተሰብን የኋላ ታሪክና እሴቶች፣ ከዛሬው ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር አስተሳስሮ የነገን አቅጣጫና ግብ የሚጠቁም፣ የህዝብን መጻኢ እድልና ተስፋ የሚያንጸባርቅ፣ ፍልስፍናዊ፣ ማህበረሰባዊ፣ ህጋዊና ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ጥቅል ሰነድ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ህገ መንግስት ከሌሎች ሰነዶች በተለየ መልኩ ጥቅል ይዘትና የቋንቋ አገላለጽ ያለው፣ ከበስተጀርባው ጥልቅ የሆነ ህጋዊ፣ ማህበረሰባዊ እና ፖለቲካዊ እሴቶችን እና መርሆዎችን ያዘለ እና በህዝቦች አንጻራዊ መግባባት ላይ የሚመሰረት ሰነድ ነው።

የህገ መንግስት ምሁራንና ፖለቲከኞች ህገ መንግስትን ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ህያው ሰነድ ነው በማለት ይገልጹታል።ይህ ማለት ግን ህገ መንግስት ልክ እንደ ሀውልት ምንም ሳይነካካና ለውጦች ሳይደረጉበት የሚዘልቅ ነው ማለት እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል። ምክንያቱም ህገ መንግሰት ከህዝቡ ችግር፣ ፍላጎት፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ቴክኖሎጂያዊ እድገቶችና ለውጦች ጋር አብሮ የሚያድገና የሚዳብር ነውና። ለምሳሌ ያህል የአሜሪካ ህገ መንግስት ላለፉት 230 አመታት ሊዳብርና ሊፋፋ የቻለው ለበርካታ ጊዜያት ትርጉም (amendment) ስለተደረገለት ነው።

ወደ እኛ ሀገር ሁኔታ ስንመጣም አሁን በስራ ላይ ያለው የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ሊዳብርና ሊሻሻል እንደሚችል በራሱ በህገ መንግስት ውስጥ በግልጽ ተደንግጓል። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ህገ መንግስት መፍትሄ መፈለጊያ መሳሪያ እንደመሆኑ መጠን አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አኳያ ህገ መንግስቱን መተርጎም ግድ የሚልበት ታሪካዊ ጊዜ ላይ ደርሰናል።

የህገ መንግስት ትርጉም ምንነትና አስፈላጊነት

ህገ መንግስት የህጎች ሁሉ የበላይ ህግ እንደመሆኑ መጠን ማንኛዉም በአንድ ሀገር የሚወጣ ህግ ፣ የባለስልጣናት ውሳኔዎች፣  ሌሎች ተግባራትና አሰራሮች ሁሉ ከህገ መንግስቱ በታች ናቸው። ይህ የሚያስገነዝበው ነገር ቢኖር ማናቸውም የበታች ህግጋትና ውሳኔዎች ከህገ መንግስቱ የሚቃረኑና የማይጣጣሙ ከሆነ ተፈጻሚነት እንደሌላቸው ነው። ከዚህ አንጻር ውሳኔ የሚወስኑ አካላት የሚወስኗቸው ህጎች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎች…ወዘተ ገና ከጅምሩ ከህገ መንገስቱ ጋር የማይቃረኑ መሆኑን የማረጋገጥ ሀላፊነት ይኖርባቸዋል። ይሁንና ህጎች በሚወጡበት ጊዜ፣ በሚተረጎሙበት ወይም ስራ ላይ በሚውሉበት ወቅት ከህገ መንግስቱ ጋር ይቃረናሉ የሚል ክርክር ሊነሳ ይችላል።

በተመሳሳም የሚወሰኑ ውሳኔዎች ከህገ መንግስቱ አጠቃላይ መንፈስና አላማ ጋር የማይጣጣሙ ወይም የሚቃረኑ ናቸው በሚል በግለሰቦች አልያም በተለያዩ አካላት ጥያቄ ሊነሳ ይችላል።

በሌላ መልኩ ህገ መንግስት በአጠቃላይ መርሆዎች ላይ የተመሰረተና ጥቅል ድንጋጌ የያዘ ሰነድ በመሆኑ አስቀድመው ያልተተነበዩ ፖሊቲካዊ፣ ማህበራዊና ሌሎች አዳዲስ ሁኔታዎች ልክ በኛ ሀገር አሁን እንዳጋጠመው ሁኔታ አተገባበሩን አስቸጋሪና ውስብስብ እንዲሆን ያደርጉታል። በዚህ ሁኔታ የህገ መንግስት ጥያቄውን አይተው ተገቢውን ውሳኔ በመስጠት የህገ መንግስቱን የበላይነት የሚያስከብሩ የህገ መንግስት ተርጓሚ አካላት መኖር አለባቸው።

እነዚህ አካላት የቀረቡትን ህገ መንግስታዊ ጥያቄዎች በከፍኛ ጥንቃቄና መሰረታዊ የአተረጓጎም መርሆችን በተከተለ እና ገለልተኛ በሆነ ሁኔታ የህግ ትርጓሜ መስጠት ይጠበቅባቸዋል።

የህገ መንግስት ትርጉም የሚሰጥ አካል በተለያዩ ሀገራት የተለያየ አወቃቀር አለው። ለምሳሌ ያህል በአሜሪካ መደበኛ ፍርድ ቤቶች፣ በስዊዘርላንድ ህዝበ ውሳኔ፣ በጀርመን ለዚሁ ጉዳይ የተቋቋመ ፍርድ ቤት ሲሆኑ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ህገ መንግስት የመተርጎም ስልጣን በህግ ተሰጥቶታል። የህገ መንግስት ትርጉም የሚሰጡ ተቋማት በመርህ ደረጃ ከመንግስት አካላት ነጻና ገለልተኛ መሆን የሚጠበቅባቸው ሲሆን የራሳቸው የሆነ የህገ መንግስት ትርጉም ስርዓትንም ይከተላሉ።

አንጋፋው የህግ ምሁርና የህገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ አባል ዶክተር ፋሲል ናሆም “የፌዴራሊዝም ትርጉምና ጽንሰ ሀሳብ” በሚል ርእስ  ለስልጠና ባቀረቡት አንደ ጽሁፋቸው ህገ መንግሰት ለተለያዩ መርሆችና አላማዎች አንደሚተረጎም ይጠቅሳሉ። ከእነዚህም ውስጥ ግልጽ ያልሆኑና የሚያወዛግቡ ጽንሰ ሀሳቦችን፣ ቃላቶችን፣ ሀረጎችን፣ አገላለጾችን፣ የህግ መንፈሶችንና የመሳሰሉትን ግልጽ ለማድረግ (clarity)፣ ግጭት ወይም ያለመጣጣም (inconsistency) በሚኖርበት ጊዜ እንዲጣጣም ለማድረግ፣ በግልጽና በዝርዝር ያልተገለጹና ያልተሸፈኑ ጉዳዮችን ክፍተቶች ለመሙላት፣ ህጎቹ አሻሚ፣ አከራካሪ ወይንም ደግሞ በአንድ ጉዳይ ላይ ምንም ያላሉ ከሆነ (Omission)፣ ህገ መንግስቱ ከጊዜው አዳዲስ ነገሮችና ሁኔታዎች ጋር እንዲሄድ ለማስቻል (dynamism) ሲያስፈልግ እንደሆነ ያስገነዘባሉ።

የህግ ባለሙያዎችና የመስኩ ምሁራን አንድና ብቸኛ የህገ መንግስት ትርጉም አሰጣጥ መንገድ እንደሌለም ይገልጻሉ። አያይዘውም አንድን የህገመንግስት ትርጉም ጥያቄ ከአንድ በላይ የሆኑ የትርጉም አሰጣጥ መንገዶችና መርሆች ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚቻልና አስፈላጊም እንደሆነ ይገልጻሉ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የህግ መምህር የሆኑት ዶክተር ጌታቸው አሰፋ የህገ መንግስት ትርጉምን አስመልክቶ ባልታተመ አንድ ጥናታዊ ጽሁፋቸው ስድስት አይነት የህገ መንግስት አተረጓጎም መንገዶች እንዳሉ ይገልጻሉ።

የመጀመሪያው የተጻፈውን የህገ መንግስት ሰነድ በመጠቀም የሚደረግ ትርጉም (Textualism) ሲሆን፣ ይህ  የሰነዱን ትርጉም ለማረጋገጥም ጥቅም ላይ ሊውል የሚገባው መንገድ የህገ መንግስቱን ቃላት ቀጥተኛ ትርጉም በመከተል መሆን አለበት የሚል እሳቤ ያለው ነው፡፡

ሁለተኛው መንገድ ደግሞ የህገ መንግስቱ አጽዳቂዎች በተረዱበት መንገድ የመተርጎም መርህ (Originalism) የሚባል ሲሆን የዚህ ዘዴ አራማጆች ህገ መንግስትን መተርጎም በሚያስፈልግበት ጊዜ አከራካሪ የሆነው የህገ መንግስት ቃል፣ ሃረግ ወይም ክፍል መተርጎም ያለበት የህገ መንግስቱ አጽዳቂዎች በሰጡት ትርጉም መሰረት መሆን አለበት የሚል እምነት አላቸው።

ሶስተኛው ዘዴ ደግሞ በቀደምት ውሳኔዎች ውስጥ በዳበሩ ቀኖናዎች ላይ የተመስረተ የትርጉም መርህ (Doctrinarism) ሲሆን፣ ይህ መርህ ባለፉት የፍርድ ቤቱ የህገ መንግስት ትርጉም ውሳኔዎች ውስጥ የተቀመሩ ህግጋትንና አመክኖዎችን በመመልከት፣ አሁንም ወደፊትም የሚያጋጠሙ ተመሳሳይ የትርጉም ጉዳዮችን በዚያው ቀኖና መሰረት መወሰን የሚሞከርበት መንገድ እንደሆነ ምሁሩ ይገልጻሉ፡፡

አራተኛው መንገድ በህገ መንግስታዊ እድገት ላይ የተመሰረተ የትርጉም መርህ (Constitutional Development) እንደሆነ የሚጠቅሱት ዶክተር ጌታቸው፤ በዚህ መንገድ የሚደረግ ትርጉም ህገ መንግስትም የሚያድግ ህግ ነው የሚል እሳቤ ያለው ሲሆን  ከ originalism ትርጉም በተቃራኒ ህገ መንግሰት በየጊዜው በሚዳብሩ ልምዶች፣ ተግባራትና የፖለቲካ ባህል ጭምር ላይ ተመስርቶ ሊያድግ ይችላል ብሎ ያምናል፡፡

አምስተኛው መንገድ ስርዓታዊ አላማ ላይ የተመሰረተ የትርጉም መርህ (Systemic Purpose) በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣የሕገ መንግስት ሰነዱን አላማ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የፖለቲካ ስርዓቱን አላማና እሴቶቹን በመመልከት የህገ መንግስት ትርጉም የሚደረግበት ዘዴ እንደሆነ ያስገነዝባሉ፡፡

ስድስተኛው መንገድ ተፎካካሪ ፍላጎቶችን በማመዛዘን የሚደረግ የሕገ መንግስት ትርጉም (Balancing) የሚባል እንደሆነ የሚያስረዱት ዶክተሩ፤ ተመጣጣኝና ተመሳሳይነት ያላቸው የህግ ድንጋጌዎች አለመጣጣም ቢታይባቸው የሚዛናዊነትና የምክንያታዊነት መርህን በመከተል ፍትሀዊ ውሳኔ የሚሰጥበት ስልት ነው።

ከላይ ከተጠቀሱት የትርጉም መንገዶች ውጭ ሌሎችም ሊኖሩ የሚችሉ መሆኑን የሚገልጹት ዶክተር ጌታቸው፣ ዋናው ቁም ነገር አንድን የህገ መንግስት ትርጉም ጥያቄ ከላይ ከተገለጹት የትርጉም መርሆዎች መካከል ከአንድ በላይ በአንድ ጊዜ ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከሀገራዊ ምርጫው መራዘም ጋር ተያይዞ በመንግስት የቀረበው የህገ መንግስት ትርጉም አማራጭ እያስነሳ ያለው አንዱ የመከራከሪያ ነጥብ በአንድ በኩል መንግስት የኮቪድ-19 ወረርሽን እንደ ምክንያት በመውሰድ ከ 2012 ዓ.ም ሀገራዊ ምርጫና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተገናኘ ያቀረበው የህገ መንግስት ትርጉም ጥያቄ ሌሎች አማራጮችን ከግምት ውስጥ ያላስገባና ስልጣንን ለማራዘም የተደረገ ዘዴ ስለሆነ ትርጉም አያስፈልገውም ወይም ግልጽ ነው የሚልና፣ በሌላ በኩል ህገ መንግስቱ አሁን እንደከሰተው አይነት ወረርሽኝ በሚያጋጥሙበት ወቅት በማይደረገው ምርጫ ሳቢያ የሚፈጠረውን የሥልጣን ክፍተትና መንግሥት አልባነት ለመፍታት ምን መደረግ እንዳለበት በህገ መንግስቱ በግልጽ ስላለተቀመጠ የህገ መንግስት ትርጉም ያስፈልጋል የሚል አቋም ነው።

ይሁንና የመጀመሪያውን ሀሳብ የማይደግፉ በርካታ ምሁራንና ፖለቲከኞች አሁን እንዳጋጠመው አይነት ወረርሽኝና ትልቅ ተጽእኖ የሚያሳድር ተመሳሳይ ሁኔታ ሲያጋጥም በኢፌዴሪ ህግ መንግስት ውስጥ ምን መደረግ እንዳለበት በግልጽና በዝርዝር ያልተሸፈኑ ጉዳዮች ወይም በአንድ ጉዳይ ላይ ምንም ሳይባል የታለፉ (Omission) ጉዳዮች በመኖራቸው ምክንያት ከነባራዊና ከተጠጨባጭ ሁኔታ በመነሳት ትርጉም መስጠት አስፈላጊና ህጋዊ እንደሆነ ያስገነዝባሉ። ከዚህ ውጪ በተለያዩ ቡድኖች እየቀረቡ ያሉ አማራጮች የህገ መንግስት መሰረት የሌላቸው ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ፖለቲካዊ ችግሮችን በይበልጥ ሊያወሳስቡ እንደሚችሉ አክለው ያስረዳሉ።

ህገ መንግስትን በመተርጎም የህግ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ሚና

በአሁኑ ጊዜ የብዙዎችን ትኩረት እየሳበ የሚገኘው የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የሚባለው ተቋም በኢፌዴሪ ህግ መንግስት አንቀጽ 82 መሰረት በ 1987 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን፣ ጉባኤው 11 አባላት እንደሚኖሩትና ስለ አባላቱ ማንነትና አመራረጥ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 2 ላይ ተዘርዝሯል። በዚሁ መሰረት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት የጉባኤው ሰብሳቢ፣ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ደግሞ ምክትል ሰብሳቢ በመሆን ሲያገለግሉ፣ በሙያ ብቃታቸውና በስነ ምግባራቸው የተመሰከረላቸው ስድስት የህግ ባለሙያዎች በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅራቢነት በሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ይሾማሉ።ቀሪዎቹ ስድስት አባላት ደግሞ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት መካከል ይሾማሉ።

በአሁኑ ሰዓት አጣሪ ጉባኤውን በፕሬዚዳንትነት እየመሩ የሚገኙት ወይዘሮ መአዛ አሸናፊ ሲሆኑ፣ አቶ ሰለሞን አረዳ ደግሞ ጉባኤውን በምክትል ፕሬዚዳንትነት እየመሩ ይገኛሉ። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅራቢነት በሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት የተሾሙ የጉባኤው አባላት  ዶክተር ፋሲል ናሆም፣ አቶ ክፍለ ጽዮን ማሞ፣ አቶ ሚሊዮን አሰፋ፣ ዶክተር ሀሺም ተውፊቅ፣  ወይዘሮ ደስታ ገብሩ እና ወይዘሮ ኡባህ መሀመድ ሲሆኑ፣ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ተሹመው እያገለገሉ የሚገኙት የጉባኤው አባላት ደግሞ  አቶ ብርሃን ሀይሉ፣ ዶክተር ቀንአ ያደታ እንዲሁም አቶ መለሰ አለሙ ናቸው።

የአጣሪ ጉባኤው ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 798/2005 እንደሚያስረዳው የህገ መንግስት ትርጉም ጥያቄዎች በሶስት አይነት መንገድ ሊቀርቡ ይችላሉ። እነዚህም በፍርድ ቤት ሊወሰን የሚችል ጉዳይ ከሆነ ስልጣን ባለው ፍርድ ቤት ቀርቦ ሲታይ፣ ስልጣን ባለው አስፈጻሚ አካል ቀርቦ የመጨረሻ ውሳኔ ሲያገኝና በፍርድ ቤት ሊወሰን የማይችል በማንኛውም ጉዳይ ላይ የህገ መንግስት ትርጉም ጥያቄ አንድ ሶስተኛ ወይም ከዛ በላይ በፌዴራል ወይም በክልል ምክር ቤት አባላት ወይም በፌዴራሉም ሆነ በክልል አስፈጻሚ አካላት ለአጣሪው ጉባኤ ሊቀርብ ይችላል።

በአጠቃላይ እነዚህ በአዋጁ ላይ የተቀመጡት የህገ መንግስት ጉዳዮች በሁለት መልኩ ለህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ሊቀርቡ ይችላሉ። እነዚህም በፍርድ ቤት ክርክር ጊዜ ሊቀርቡ ይችላሉ። ወይንም ከፍርድ ቤት ውጪ ቀጥታ ሊቀርቡ ይችላሉ።

በፍርድ ቤት በተያዙ ጉዳዮች ህገ  የመንግስት ትርጉም ጥያቄ የተነሳ እንደሆነ ጥያቄው ጉዳዩን በያዘው ፍርድ ቤት ወይም በባለጉዳዩ ለአጣሪ ጉባኤው ሊቀርብ ይችላል።  ፍርድ ቤቶች ይህን የሚያደርጉት በያዙት ጉዳይ ላይ ለመወሰን የህገ መንግሥት ትርጓሜ ያስፈልጋል ብለው ሲያምኑ ብቻ እንደሆነና ፍርድ ቤቶችም ሆኑ ባለጉዳዮች ጉዳዩን ሲያቀርቡ ለትርጉም አስፈላጊ የሆነውን ነጥብ ብቻ  እንደሚልኩ ተደንግጓል፡፡ ይህም ሲሆን አጣሪ ጉባኤው ከፍርድ ቤት የተላከለትን የትርጉም ጥያቄ መርምሮ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ጉዳዩ በእንጥልጥል እንዲቆይ ሊያዝ እንደሚችል ተደንግጓል።

በመንግስት አካል ወይም ባለስልጣን በተሰጠ የመጨረሻ ውሳኔ መሰረታዊ መብቴና ነጻነቴ ተጥሷል በሚል በግለሰብ የሚቀርበው አቤቱታ ገዳዩን አይቶ ለመወሰን በየደረጃው ስልጣን ላለው የመንግስት አካል ቀርቦ የመጨረሻ ውሳኔ ያገኘ ከሆነ ነው።

ከላይ በተጠቀሱት አግባቦች ለአጣሪ ጉባዔው የሚቀርቡ ጥያቄዎች ዘርዘር ባለ ጽሑፍ መቅረብ የሚገባቸው ሲሆን በህገ መንግሰት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ አዋጅ 798/2005 አንቀጽ 9 መሰረት ጉባዔው ትርጓሜ ከመስጠቱ አስቀድሞ አግባብነት አላቸው ብሎ የሚያምንባቸውን ተቋማት ወይም ባለሙያዎች ቀርበው አስተያየት እንዲሰጡ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ጉባኤው አስፈላጊ ነው ብሎ ያመነበትን ማንኛውንም አይነት ማስረጃ አስቀርቦ ሊመረምር ወይም ባለሙያ ጠርቶ ሊጠይቅ እንደሚችል በዚሁ አዋጅ ተደንግጓል።

በዚሁ መሰረት አጣሪ ጉባኤው ከ6ኛው ዙር ብሔራዊ ምርጫ ጋር ተያይዞ በቀረበው የህገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ላይ ከዚህ ቀደም ባልታየ ሁኔታ የባለሙያዎችን እና ህገ መንግስቱ ሲረቅና ሲጸድቅ የተሳተፉና ሙያዊ እገዛ ያደረጉ አካላትን በቀጥታ በሚተላለፍ የቴሌቪዥን ስርጭት ሀሳብና የህግ ትንታኔያቸው የሚደመጥበት ሶስት ተከታታይ መድረኮችን/ስነ ስርአቶችን (hearing) አዘጋጅቶ ግብአቶችን ሰብስቧል።

በርካቶች ይሄ ሂደት ለአገሪቱ የዴሞክራሲ ሂደት ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን በመግለጽ፣ አሳታፊና ለሕዝብ ግልጽ በሆነ አግባብ መታየቱንም አድንቀዋል። በአንጻሩ ለየት ያሉና በተቃራኒው የቆሙ ድምፆች አለመሰማታቸው ቅር እንደሚያሰኝና ሂደቱንም እንከን የለሽ ነበር ማለት እንደማይቻል  ይናገራሉ፡፡

ከእነዚህ መድረኮች በአንዱ ተጋብዘው ሙያዊ ትንታኔያቸውን ያቀረቡት የህግ ምሁሩ አቶ ደበበ ሀይለገብርኤል ባሁኑ ወቅት ከ2012 ምርጫ ጋር ተያይዞ ለህገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ የቀረበው የትርጉም ጥያቄ ከዚህ በፊት ይቀርቡ ከነበሩት የትርጉም ጥያቄዎች በተወሰነ ደረጃ እንደሚለይ ይገልጻሉ። እንደርሳቸው አባባል ጉዳዩ ግዙፍ ህገ መንግስታዊ ጥያቄ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከምክር ቤቱ ጀምሮ ከፍተኛ የሆነ ውይይት እንዲቀሰቀስ ማድረጉ፣ የበርካቶች የመወያያ አጀንዳ ሊሆን መቻሉ፣ በመንግስት ስራ የህዝብን ተሳትፎና ግንዛቤ ለማሳደግ በአጣሪ ጉባኤው የተወሰደው ተነሳሽነት ሂደቱን ልዩ እንደሚያደርገው ይገልጻሉ።

አያይዘውም እንደዚህ አይነት መድረክ ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ ላይ እንዲሳተፉ እድል የሚሰጥ በመሆኑ፣ መንግሰት የሚሰራቸውን ስራዎች በግልጽነትና በተጠያቂነት እንዲያከናውን በር የሚከፍት በመሆኑ፣ የስነ ህግ ፍልስፍናን የሚያሳድግ በመሆኑ፣ የህገ መንግስትን ባህል ለማዳበር ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር በመሆኑ፣ የጉባኤውን አባላትና የሌላውንም ህብረተሰብ እውቀት የሚጨምር መሆኑና ጥርጣሬንና አሉባልታን የሚያጠራና የሚያስወግድ በመሆኑ ያላቸው አንደምታ ቀላል እንደማይባል ያብራራሉ።

በሌላ በኩል አጣሪ ጉባኤው የቀረበለትን የህገ መንግስት ትርጉም ጥያቄ ገለልተኛ ሆኖ ከማየት አኳያ ከብዙ ወገኖች የሚነሳውን ጥያቄና ጥርጣሬ በተመለከተ አስተያየተቸውን ሲሰጡ፣ እንዲህ አይነቱ ጥርጣሬና እምነት የማጣት ሁኔታ ከለውጡ በፊት ከነበረው ሁኔታ በመነሳት ሊኖር እንደሚችል በመጥቀስ፤ ይህም ሆኖ በዚህ ታሪካዊ ጊዜ ጉባኤው ለህግ ልእልናና ለህግ የበላይነት ከመቼውም ጊዜ በላይ በመቆም ተቋማዊ ልእልናውን ሊያስመሰክር እንደሚገባ ያስገነዝባሉ።አክለውም የአጣሪው ጉባኤ አባላት ለህሊናቸውና ለህገ መንግስቱ ተገዢ ሆነው ትክክለኛ ነው ብለው የሚያስቡትን ይሰጣሉ ብለው እንደሚያስቡ ይገልጻሉ።

የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔው ውሳኔ በተባበረ ድምፅ በሁሉም አባላት ድጋፍ ወይም በስብሰባው በተገኙ አባላት አብላጫ ድምፅ የሚተላለፍ ሲሆን፣ የተሰጠው ድምፅ በሁለቱም ወገን እኩል በሚሆንበት ጊዜ ሰብሳቢዋ ያሉበት ወገን ወሳኝ ይሆናል፡፡

በኢፌዴሪ ህገ መንግስት ድንጋጌ መሰረት ለሚቀርቡ የህገ መንግስት ትርጉም ጥያቄዎች ውሳኔ የመስጠት ስልጣን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው። በህገ መንግሰት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ አዋጅ 798/2005 እንደተቀመጠው የአጣሪ ጉባኤው ስልጣን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለሚሰጠው ውሳኔ የሚያግዝ የውሳኔ ሀሳብ ማቅረብ ነው። በዚህ መልኩ አጣሪ ጉባኤው የቀረበለትን የህገ መንግሰት ትርጉም ጥያቄ መርምሮ ትርጉም አያስፈልገውም ብሎ ካመነ ለባለጉዳዩ ወይም ከፍርድ ቤት የመጣ ከሆነ ደግሞ ለፍርድ ቤቱ ተመላሽ ያደርጋል።

ስለሆነም አሁን ከቀረበው የምርጫ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ጉባኤው ትርጉም ለመስጠት ስልጣን አለው ወይስ የለውም ለሚለው እና የቀረበው ጥያቄ የህገ መንግስት ትርጉም አያስፈልገውም ተብሎ በተለያዩ አካላት ለሚነሳው ክርክር ጉባኤው የራሱን የውሳኔ ሀሳብ ከጉዳዩ ጋር የተያያዙ መረጃዎችንና ሰነዶችን አያይዞ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ይልከዋል ተብሎ ይጠበቃል።

ለአጣሪው ጉባኤ የሚቀርቡ ጉዳዮች የተለየ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ገብቶ በቅድሚያ እንዲታይ በጉባኤው ሰብሳቢ ካልተወሰነ በስተቀር እንደ አቀራረባቸው ቅደም ተከተል ማጣራት እንደሚደረግባቸው በአዋጅ 798/2005 አንቀጽ 10 ላይ ተደንግጓል። አንድ ጉዳይ በሚታይበት ጊዜ በበቂ ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ለተደጋጋሚ ቀጠሮ እንደማይተላለፍም በአዋጁ ተገልጿል።

ከዚህ አኳያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበው የትርጓሜ ይሰጥበት ጥያቄ ግዙፍ የህገ መንግስት ጥያቄና ፈጣን ምላሽ የሚጠይቅ ጉዳይ በመሆኑ በጥቂት ጊዜ ውስጥ መልስ ያገኛል ተብሎ ይገመታል። እስካሁን ባለው አሰራር ከፍርድ ቤት ተመርተው የመጡ በተለይም ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው የሚከታተሉ፣  እግድ የተጠየቀባቸው ጉዳዮች፣ የህጻናት ጉዳዮችና የመሳሰሉት ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እንደሚታዩ ከአጣሪው ጉባኤ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ለአጣሪው ጉበኤ የሚቀርብ አቤቱታ ከቀረበ በኋላ በአዋጁ አንቀጽ 8 መሰረት የጉባኤው ሰብሳቢ በቀረቡ ጉዳዮች ላይ የሙያ አስተያየት እንዲዘጋጅ ለንኡስ አጣሪ ኮሚቴ አባላት ወይም ለጽህፈት ቤቱ ባለሙያዎች በቅድሚያ ይመራል። ምንም እንኳን ንኡስ አጣሪ ኮሚቴው የህገ መንግስት እውቅና ባይኖረውም ለጉባኤው ስራ መቀላጠፍ በሚል በአዋጁ አንቀጽ 24(2) መሰረት የተደራጀ ነው። በዚህ ድንጋጌ መሰረት ንኡስ አጣሪ ኮሚቴው ሰብሳቢውን ጨምሮ በአጣሪ ጉባኤው የሚሰየሙና በአጣሪ ጉባኤው ውስጥ በቋሚነት የሚሰሩ ሶስት አባላት አሉት።

በህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ አዋጅ 798/2005 አንቀጽ 14 መሰረት ለህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ አቤቱታ የሚቀርበው በሌሎች መደበኛ ፍርድ ቤቶች እንደሚታየው በክፍያ ሳይሆን በነጻ እንደሆነ ይደነግጋል። የዚህም ምክንያት አጣሪ ጉባኤው ስራውን የሚሰራው ለህዝብ ጥቅምና ህገ መንግስቱን የበላይነት ለማስጠበቅ ነው ተብሎ ስለታመነ ነው።

የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤው ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ደሳለኝ ወየሳ ባለፉት አመታት አጣሪ ጉባኤው ስራውን ሲያከናውን የነበረበት ሂደት አልጋ በአልጋ በሚባል ሁኔታ እንዳልነበረ በመጥቀስ ከዚህ ጋር ተያይዞ ከህብረተሰቡ የሚቀርቡ አንዳንድ ትችቶች እውነታነት እንዳላቸው ይናገራሉ። ሀላፊው በቅርቡ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ በሰጡት ቃለ መጠይቅ እንደ ችግር ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል በአጣሪ ጉባኤው ላይ ያለው የስራ ጫና አንዱ እንደሆነ ይናገራሉ።

ይህንን ጉዳይ ሲያብራሩ ለጉባአኤው የሚቀርቡ ጥቄዎች በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በፍርድ ቤት ታይተው የመጨረሻ ውሳኔ ያገኙ ናቸው። ነገር ግን ጥያቄዎቹ አብዛኛውን ጊዜ ማለት በሚቻል ሁኔታ የህገ መንግስት ትርጉም ምንነትን መሰረት አድርገው የሚቀርቡ እንዳልሆኑና የጥያቄዎቹ ይዘትም አጣሪ ጉባኤውን እንደ አንድ ይግባኝ ሰሚ አካል አድርጎ የመመልከት ችግር እንደሚታይ ያብራራሉ።

ከዚህ ጋር ተያይዞ እንደ ችግር የሚነሳው ነገር ለአጣሪ ጉበኤው የሚቀርቡ የህገ መንግስት ትርጉም ጉዳዮች ምንነትና ይዘት በህጉ ላይ ግልጽ ሆነውና ተዘርዝረው የተደነገጉ ባለመሆኑ በጉባኤው ስራ ላይ ከባድ ፈተና መሆኑ ነው።

የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የህግ ምሁር ዶክተር ጌታቸው አሰፋ አጣሪ ጉባኤው የህገ መንግስት ትርጉም የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ ብቻ ትኩረት አድርጎ እንዲሰራ በባለጉዳዮች የሚቀርቡ ጉዳዮችን የሚያጣሩና የጉባኤውን ስራ የሚያቀሉ ንኡሳን ኮሚቴዎችን ማዋቀር እንደሚያስፈልግ ያነሳሉ። የጀርመንና የደቡብ አፍሪካን ተመሳሳይ የህገ መንግስት ትርጉም ተቋማት ተሞክሮን በማጣቀስ፣ ተሞክሮዎቹ ተወስደው ተግባራዊ ቢደረጉ በአጣሪ ጉባኤው ላይ ያለውን የስራ ጫና በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ እንደሚቻል ይገልጻሉ።

ሌላው ከአሰራር ጋር በተያያዘ እንደ ክፍተት የሚነሳው ነገር አጣሪ ጉባኤው የያዘውን ጉዳይ የሚያይበት መንገድ ነው። ይህም በህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ አዋጅ 798/2005 አንቀጽ 4 መሰረት ጉባኤው የያዘውን ጉዳይ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 12(1) መሰረት ለህዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ ሊያይ እንደሚችል ተደንግጓል። ነገር ግን በተግባር ጉባኤው ጉዳዮችን ግልጽ በሆነ መንገድ እያየ እንዳልነበረ አጠያያቂ ጉዳይ አይደለም።ይሁንና ባሁኑ ወቅት ጉባኤው ከ2012 ምርጫ ጉዳይ ጋር ተያይዞ የቀረበለትን የህገ መንግስት ትርጉም ጥያቄ ለመመለስ እየሄደበት ያለው ግልጽና አሳታፊነት የሚታይበት ሂደት እንደ ጥሩ ጅምር የሚታይና የሚበረታታ እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል።

ከአሰራር ጋር በተያዘ እንደ ክፍተት የሚነሳው ሌላው ነጥብ በአዋጁ ላይ የህገ መንግስት ትርጉም እንዲሰጥለት ከሚያቀርበው ባለጉዳይ ውጪ ሌላኛው ተከራካሪ ወገን በጉዳዩ ላይ የራሱን መከራከሪያ ለጉባኤው የሚያቀርብበት እድል ያለመኖሩ ነው።

ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ጉባኤው አስራ አንድ አባላት አሉት። የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት እና ምክትል ፕሬዚዳንት በጉባኤው ውስጥ በሰብሳቢነት እና በምክትል ሰብሳቢነት ይሰራሉ።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ፕሬዚዳንቱና ምክትል ፕሬዚዳንቱ በጉባኤው ውስጥ መስራታቸው በሁለቱም ቦታ ተመሳሳይ ሰዎች ሆነው መስራታቸው ገለልተኝነት የሌለው አሰራር ይሆናል የሚል ሀሳብ ከአንዳንድ የህግ ባለሙያዎችና ፖለቲከኞች ይቀርባል። በሌላ በኩል ሰብሳቢውና ምክትል ሰብሳቢው የዲስፕሊን ጉድለት ወይም ስራ ላይ የብቃት ማነስ ቢያሳዩ ጉዳዩ በምን አግባብ እንደሚታይ በህጉ ላይ ግልጽ ሆኖ አልተቀመጠም የሚል ትችት ይቀርባል።

በአጠቃላይ ከላይ የተነሱት ነጥቦች የሚያሳዩት ነገር ቢኖር የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ተስፋ የሚሰጡ ለውጦችንና የሚበረታቱ የአሰራር ሂደቶችን እያደረገ እንደሆነ ሁሉ፣ ከህግ፣ ከአደረጃጀትና ከአተገባበር አኳያ ችላ ሊባሉ የማይገቡ ክፍተቶችም እንዳሉበት ነው።

በመሆኑም አሁን ያለውን የለውጥ አጋጣሚ እንደ ትልቅ እድል በመጠቀም አጣሪ ጉባኤው ህብረተሰቡ በተቋሙ ላይ ያለውን አመኔታ እንዲያሳድግ ማድረግ ይጠበቅበታል። ለዚህም ጉባኤው ከአሰራር፣ ከአደረጃጀትና ከህግና ከሌሎችም አኳያ የሚታዩበትን ክፍተቶች በማሻሻል ስራውን በሙሉ አቅምና በተደራጀ መልኩ ሊሰራ ይገባል እንላለን።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም