በአማራ ክልል ከአንድ ሺህ በላይ ያለዕድሜ ጋብቻዎች እንዲቋረጡ ተደረገ

123

ባሕርዳር ግንቦት 16/2012 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ሕግን በመተላለፍ ሊፈጸሙ የነበሩ ከአንድ ሺህ በላይ ያለዕድሜ ጋብቻዎች  እንዲቋረጡ መደረጉን የክልሉ ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ሰላማዊት ዓለማየሁ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ ሕፃናትን ያለ ዕድሜያቸው የመዳር ጎጂ ልማድ ለማስቀረት በተደረገው ጥረት እየቀነሰ መጥቶ ነበር።

ሆኖም በዚህ አስቸጋሪ ወቅትም የልጅነት ጋብቻ እየተካሄደ መሆኑን አመልክተው፤ በተያዘው ዓመት አንድ ሺህ 70 የልጅነት ጋብቻዎች ከወላጆች ጋር በመነጋገር እንዲቋረጡ መደረጉን አስታውቀዋል።

በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የትምህርት ቤቶች መዘጋት ወላጆች እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ደግሞ 585 ያለዕድሜ ጋብቻዎች መፈጸማቸውን ጠቁመዋል።

የትምህርት ተቋማት መዘጋትና ልጆች በቤት ውስጥ መዋል ያለዕድሜ ጋብቻ የመስፋፋት አዝማሚያ እንደሚስተዋል  ወይዘሮ ሰላማዊት ተናግረዋል።

ምሥራቅ ጎጃም፣ ደቡብ ጎንደር፣ ሰሜንና ደቡብ ወሎ ዞኖች ያለዕድሜ ጋብቻው በስፋት የተስተዋለባቸው አካባቢዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

“ልጆች ያለዕድሜያቸው ሲዳሩ ለተለያዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ይጋለጣሉ፤ የወደፊት ሕይወታቸው አስቸጋሪ ያደርገዋል”ብለዋል።

ለድርጊቱ መባባስም በየደረጃው የተቋቋመው የጎጂ ልማዳዊ ድርጊት አስወጋጅ ኮሚቴ ጥምረት ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ የሚጠበቅበትን ያህል ባለመሥራቱ እንደሆነም ጠቁመዋል።

በክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ  የሰብአዊ መብት ጉዳዮች ተወካይ ዳይሬክተር አቶ ፀሐይነህ አጥናፍ በበኩላቸው የልጅነት ጋብቻን በ2017 ዓ.ም  ለማስቆም እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ሆኖም ከኮሮና ቫይረስ መከሰት ጋር ተያይዞ የትምህርት ቤቶች መዘጋትና በየጊዜው ይሰጥ የነበረው ጥቆማ እየተቀዛቀዘ መምጣት ችግሩ እንደገና መመለሱን ተናገረዋል።

ሕጉን ተላልፈው የልጅነት ጋብቻ ፈጽመው በተገኙ ወላጆች ላይ አስተማሪ የሆነ ቅጣት እንዲያገኙ ቢሮው በተዋረድ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

ለአቅመ አዳም የደረሰ ወንድ ልጃቸውን ግን የአስቸኳይ አዋጁን በማይጥስ መልኩ ድግሱን በመተው ጋብቻ እንዲፈጽም ማድረጋቸውንም የተናገሩት ደግሞ  በምሥራቅ ጎጃም ዞን ሸበል በረንታ ወረዳ የሞዠንና አካባቢው ቀበሌ አርሶ አደር ጌትነት ጋሻው ናቸው።

ዕድሜያቸው ለጋብቻ ያልደረሱ ልጆችን መዳር በሕግ የሚያስጠይቅ በመሆኑ ይህንኑ ተግባር አለመፈጸማቸውን ገልጸዋል።

ባለፈው ዓመት በክልሉ ሊፈፀም የነበረ ሁለት ሺህ 556 የልጅነት ጋብቻ መቋረጡንና 403 ጋብቻ ደግሞ በሕገወጥ መንገድ መፈጸሙን ከሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮው  የተገኘው መረጃ ያመለክታል።