በደብረ ብርሃን በቫይረሱ የሚፈጠር ውጥረትን ለመቀነስ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ተጀመረ

492

ደብረ ብርሀን ግንቦት 16/2012 (ኢዜአ) በደብረ ብርሃን ከተማ ኮሮናን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የሚፈጠር ውጥረትን ለመቀነስ የሚረዳ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ተጀመረ።

የአካል ብቃት እንቅስቃሴው የተጀመረው በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ ሲሆን ያዘጋጀውም የአካባቢው ኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አባል የሆነው ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ  ነው።

በዩኒቨርሲቲው የስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል አስተባባሪ አቶ ቴዎድሮስ አበሩ እንደገለጹት በጋራ ቤቶች መኖሪያ አካባቢ በየሳምንቱ ማክሰኞና ቅዳሜ   የሚቀጥል ነው።

በዚህም ነዋሪዎች ሳይንስን መሰረት ያደረገ የአካል እንቅስቃሴ ርቀትን በመጠበቅና በየቤታቸው በር ላይ ሆነው እንዲሰሩ ለማስቻል  ፕሮግራም ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር ተገብቷል።

አስተባባሪው እንዳሉት የአካል ብቃት እንቅስቃሴውም በጋራ መኖሪያ ቤት ውስጥ አብዛኛውን  ጊዜ የሚያሳልፉ የህብረተሰብ ክፍሎችን አእምሯዊ፣ አካላዊና ስነ ልቦናዊ ጥንካሬን ማጎልበት ይገባል።

 ነዋሪዎች ብዙውን ጊዜ ከቤት ውስጥ ከማሳለፋቸው የተነሳ የሚፈጠር ድብርት፣ ጭንቀትና ሌሎች ተጽዕኖዎችን ለመቀነስም ያግዛቸዋል።

ከአካል እንቅስቃሴው በተጓዳኝ  ስለኮሮና መከላከያ መንገዶች ለህብረተሰቡ በማስገንዘብ አሁን የሚስተዋለውን መዘናጋት እንዳይኖር ተነሳሽነትን ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስተባባሪው ገልጸዋል።

በከተማው በቀበሌ ሰባት “ህብር የጋራ መኖሪያ ቤት” ነዋሪ የሆኑት አቶ ፀሐይ ኃይለ ማሪያም በሰጡት አስተያየት በተጀመረው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መሳተፋቸውን ተናግረዋል።

በዚህም  ርቀትንና ንጽህናን በመጠበቅ የኮሮና ቫይረስን መከላከል እንደሚቻል ትምህርት ማግኘታቸውንም አመልክተዋል።

ወይዘሮ ወይንሸት ጥላሁን በበኩላቸው የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ ሙሉ ጊዜያቸውን በቤት ውስጥ እያሳለፉ እንደሚገኙ  ገልጸዋል።

ከቤት ውስጥ በመዋላቸው ከበሽታው አስፈሪነት ጋር ተዳምሮ በአእምሯቸው ላይ ጫና  እንዳሳደረባቸው  ጠቅሰው “የአካል እንቅስቃሴ መጀመሩ ትልቅ መፍትሄ ነው” ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ ለመጀመሪያ ጊዜ ትናንት በድምጽ ማጎያ በመታገዝ ባዘጋጀው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከ500 በላይ ነዋሪዎች መሳተፋቸው ታውቋል።