ኢትዮጵያ የሕዳሴውን ግድብ የውሃ ሙሌት በተያዘለት ጊዜ ለማካሄድ ማቀዷ ትክክለኛ ውሳኔ ነው

61

አዲስ አበባ ግንቦት 16/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የሕዳሴውን ግድብ የውሃ ሙሌት በተያዘለት ጊዜ ለማካሄድ ማቀዷ ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው ፖለቲከኞች ገለጹ፡፡

አባይ ከኢትዮጵያ ምድር የሚፈልቅ ሃብት በመሆኑ ኢትዮጵያውያን በወንዙ የማንንም ፈቃድ ሳንጠይቅ በነጻነት መጠቀም ይኖርብናልም ብለዋል።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር /ኦነግ/ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ቀጄላ መርዳሳ እና የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀ-መንበር አቶ ትዕግስቱ አወል በግድቡ ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ፖለቲከኞቹ እንዳሉትም ግብጾች በአባይ ወንዝ የበለጠ የመጠቀም ዓላማ እንጂ ያለውን እናጣለን የሚል ስጋት እንደሌላቸው ገልጸዋል።  

እንደ አቶ ቀጄላ አስተያየት ግብጾች ከዚህ ቀደም በአባይ ወንዝ ላይ ከሰሩት ልማት በተጨማሪ አሁንም ኢንዱስትሪ፣ ሜካናይዜሽንና እርሻን የመሳሰሉ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ላይ ይገኛሉ።

"ግብጾች ኢትዮጵያ ግድብ የምትገነባ ከሆነ እንጎዳለን የሚል ፍራቻ በውስጣቸው ስላለ በኢትዮጵያ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጫና ለማሳደር ይሞክራሉ" ብለዋል።

በኢትዮጵያ በኩል በግድቡ ላይ ፍትሃዊ ተጠቃሚ የመሆን ዓላማ እንጂ ግብጽን የመጉዳት ፍላጎት አለመኖሩን በመጥቀስ።

የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀ-መንበር አቶ ትዕግስቱ አወል በበኩላቸው በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ ለሚካሄድ ማንኛውም ነገር አፍሪካዊ መፍትሄ ማምጣት ይገባል ይላሉ።

የኢትዮጵያ መንግስት በግድቡ ዙሪያ ሃላፊነቱን ለመወጣት እያደረገ ስላለው ጥረት አውስተው ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ከተፋሰሱ አገራት ጋር ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማጠናከር እንዳለበት አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ በዜጎቿ አስተዋፅኦ የምትገነባው የሕዳሴው ግድብ ሉአላዊነቷን የምታስከብርበት ስለሆነም በአቋሟ መጽናት እንደሚኖርባት አቶ ቀጄላ መርዳሳ በሰጡት አስተያየት ጠቁመዋል።  

ኢትዮጵያ በመጪው ክረምት ግድቡን ውሃ ለመሙላት መዘጋጀቷን ተከትሎ ግብፅ ጫና ለመፍጠር መሞከሯ ተቀባይነት እንደሌለውም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የሕዳሴውን ግድብ የውሃ ሙሌት በተያዘለት ጊዜ ለማካሄድ ማቀዱ ትክክለኛ ውሳኔ እንደሆነም ገልጸዋል።

አቶ ቀጄላ ግብጾች ጫና ይፈጥራሉ ተብሎ የውሃውን ሙሌት ከመጀመር ወደኋላ ማለት አያስፈልግም ነው ያሉት።  

በህዝብ ተሳትፎ እየተገነባ የሚገኘው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት በመጪው ሐምሌ 2012 ዓ.ም ይጀመራል።

የግድቡ ግንባታም 73 በመቶ ተከናውኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም