ኢትዮጵያ የአባይን ወንዝ የመጠቀም መብቷን ለማስከበር የዲፕሎማሲ ስራ ማጠናከር አለባት - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የአባይን ወንዝ የመጠቀም መብቷን ለማስከበር የዲፕሎማሲ ስራ ማጠናከር አለባት

አርባ ምንጭ ግንቦት 16/2012 (ኢዜአ ) ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝ የመጠቀም መብቷን ለማስከበር በዲፕሎማሲው መስክ የምታካሂደውን ስራ አጠናክራ መቀጠል እንዳለባት በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናገሩ።
ከምሁራኑ መካከል የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳምጠው ዳርዛ ለኢዜአ እንዳሉት ለአባይ ግድብ ግንባታ ህዝቡ እንደወትሮ ሁሉ እስኪጠናቀቅም አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ እያሳየ ያለው ተነሳሽነተ ተገቢ ነው፡፡
ግብጽ ከጅማሬው አንስቶ ጭፍን ተቃውሞ ብታሰማም ኢትዮጵያ መብቷን ለማስከበር ግንባታውንና የውሀ ሙሌቱ ሳታስተጓጉል ጎን ለጎን በዲፕሎማሲው ላይ አተኩራ የምታካሄደው ስራ ማጠናከር እንዳለባት ተናግረዋል።
ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀምን በተመለከተ ግልጽ ዓለም አቀፋዊ ድንጋጌዎች መኖራቸውንና የኢትዮጵያ ህዝብ የአባይን ወንዝ የመጠቀም መብቱ ሊከበር ይገባል ብለዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም በተመለከተ ባደረገው ስምምነት መሠረት የተፋሰስ ሀገራት ፍትሃዊ አጠቃቀም መርህን ተከትለው ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ የሚደነግግ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የተፋሰስ ሀገራት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፍላጎቶች፣ መልክአ ምድራዊ አቀማመጥ ሁኔታ እንዲሁም የአንዱ መጠቀም በሌላኛው የተፋሰስ ሀገር ላይ የጎላ ተጽዕኖ አለማሳረፉን በመስፈርትነት አካቶ የያዘ እንደሆነ አመልክተዋል።
በነዚህ ድንጋጌዎች መሰረት ኢትዮጵያ የአባይን ወንዝ አልምታ የመጠቀም መብት እንዳላት አስረድተዋል።
የህግ ምሁሩ አቶ ኃይሉ ቦጋለ እንዲሁ ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን ገድባ የመጠቀም ዓለም አቀፋዊ መብት እንዳላት ተናግረዋል፡፡
ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ተሳትፎ ሳይኖር ግብጽና ሱዳን ለብቻ ያደረጉት ስምምነት ኢ-ፍትሃዊ መሆኑን ጠቅሰው "የሌላውን ጥቅም እስካልተጋፋን ድረስ አባይን ገድበን መጠቀም እንችላለን "ብለዋል።
አለም አቀፍ ህጉ ፍትሀዊነትን መሰረት ያደረገ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ኃይሉ በቅኝ ግዛት ጊዜ የተፈረመ ስምምነትን ለማጽናት መራወጥ ቅኝ ተገዢነት መሆኑን ገልጸዋል።
"የግድቡ መጠናቀቅ የኢትዮጵያን ህዝብ ከድህነት የመውጣት ጉዳይ ነው" ያሉት ደግሞ ሌላኛው የህግ ምሁር አቶ መኩሪያ ፈለሃ ናቸው።
ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን በሚጋፋ መልክ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ተገቢ ያልሆነ ተግባር እየፈጸሙ መሆኑን ሊያውቁት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
"ግብጽ በአባይ ወንዝ ላይ ግዙፉን የአስዋን ግድብ በመገደብ እስከዛሬ ስትጠቀም ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ ስምምነት አንፃር አልከለከለቻትም" ያሉት አቶ መኩሪያ መንግስት በዲፕሎማሲው መስክ የሚያካሄደውን ስራ አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለባት ተናግረዋል፡፡