የግብርና እድገት የሚረጋገጠው በመንግስት የሚሰጠው ቴክኖሎጂ ከግል ዘርፉ ጋር መደጋገፍ ሲችል መሆኑ ተገለጸ

85

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 15/2012  ዓ.ም ( ኢዜአ) የግብርና እድገት የሚረጋገጠው በመንግስት የሚሰጠው ቴክኖሎጂ ከግል ዘርፉ ጋር መደጋገፍ ሲችል መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አመለከተ።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሳኒ ረዲ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳመለከቱት፤ የግብርናውን ዘርፍ ወደ ሚፈለገው ደረጃ ለማድረስ በመንግስት ብቻ የሚከናወኑ ተግባራት ውጤት ሊያመጡ አይችሉም ።

በመሆኑም በምርምር፣ በቴክኖሎጂ ብዛትና ስርጭት፣ በኤክስቴንሽንና በሌሎች መስኮች የግል ተቋማት ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

''ለዚህ ውጤታማነት ደግሞ መንግስት በዘርፉ ያሉትን ሕጎች በመፈተሽ ላይ ነው'' ብለዋል።

የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን አስመልክቶ ግብርናው ያለበት ደረጃ ዝቅተኛ በመሆኑ የግል ዘርፉ ተዋናዮች ተሳትፎን ለማሳደግ የሚያስችሉ መደላድሎች እንዲፈጠሩ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የግብርና ዘርፉ በቀጣይነት ሊያድግ የሚችለውም ያልተቋረጠ የቴክኖሎጂ ሽግግር ሲኖር እንደሆነም አመልክተዋል።

በአገሪቱ በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሩ ጥቅም ላይ የሚያውለው ምርጥ ዘር 30 በመቶ ቢሆንም በሚፈለገው መጠን ውጤታማ ሊያደርገው እንዳልቻለ ገልጸዋል።

በመሆኑም በዘርፉ ቴክኖሎጂን ያካበቱ አለም ዓቀፍ ኩባንያዎች እንዲገቡ ማድረግ ያስፈልጋል።

ለዚህ ደግሞ አዋጆችን በማሻሻል አለም ዓቀፍ  ኩባንያዎች ከአገር ዓቀፍ አምራቾች ጋር እንዲሰሩ ለማድረግ እየተሞከረ መሆኑን አንስተዋል።

የግብርና ዕድገት ሊረጋገጥ የሚችለው የመንግስት የቴክኖሎጂ ድጋፍ ከግል ዘርፉ ጋር መደጋገፍ ሲችል በመሆኑ ወደ ተግባር ለመግባት የሚያስችሉ የህግ ማዕቀፎች እየታዩ እንደሆነ አቶ ሳኒ ጠቁመዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር በላይ ስምአኒ በበኩላቸው ''የግብርና ዘርፍ በተወሰነ ደረጃ እያደገ ቢመጣም አገሪቷ የምግብ ሉአላዊነቷን ማስከበር አልቻለችም'' ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ ዘርፉ በጣም የተወሳሰበና ፈርጀ ብዙ ጫናን የተሸከመ ሲሆን በሚፈለገው መልኩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ያለመጠቀም ዋነኛ ችግር መሆኑን አስረድተዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን የዝናብ መጠን መዛባት የጎላ ጫና እንዳያስከትል ያለውን የአስተራረስና አመራረት ዘዴ እንዲሁም የቴክኖሎጂ አጠቃቀም መፈተሽ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የቴክኖሎጂ ሽግግር ውጤታማ እንዲሆንም የአገሪቱን የግብርና ፖሊሲ ማእቀፍ ማስተካከል እንደሚገባም ነው ፕሮፌሰሩ የጠቆሙት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም