በአሶሳ ለ300 አቅመ ደካሞች ድጋፍ ተደረገ

64

አሶሳ ፣ ግንቦት 15/ 2012 ዓ.ም. (ኢዜአ) በአሶሳ ከተማ የሚገኙ የመንግስት ተቋማትና የበጎ አድራጎት ማህበራት ለ300 ችግረኛ ወገኖች ድጋፍ አደረጉ ።

በከተማው የሚገኙ የመንግስት ተቋማትና በጎ አድራጎት ማህበራት ከ700 ሺህ ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገዙ የምግብና ምግብ ነክ ቁሳቁሶች ድጋፍ አድርገዋል ።

የአሶሳ ከተማ አስተዳደር፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስፖርት ኮሚሽንና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ድጋፍ ያደረጉ የመንግስት ተቋማት ሲሆኑ ኢትዮ-ድንበር ተሻጋሪ እና የደወልሽ ይሰማ በጎ አድራጎት ማህበራትም ተሳታፊዎች ናቸው ።

የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባና የከተማው ኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ ሃይል ሰብሳቢ አቶ ኡመር አህመድ በወቅቱ እንዳሉት አስተዳደሩ አዋጁን ተግባራዊ በማድረግ ቫይረሱ በከተማው እንዳይዛመት የመከላከል ጥረት እየተከናወነ ይገኛል ።

የቫይረሱ ስርጭት እየከፋ ከመጣ አቅመ ደካሞችና ደጋፊ የሌላቸው ወገኖች ላይ ተፅእኖው እንዳይበረታ ለመከላከል ምግብና ሌሎች ድጋፍን የማሰባሰብ ስራ እየተካሔደ መሆኑን አስረድተዋል ።

"መልካም ነገር ማድረግ ለራስ ነው " የሚለው የኢትዮ ድንበር ተሻጋሪ በጎ አድራጎት ማህበር አስተባባሪ ወጣት አማኑኤል ተስፋዬ ሁሉም ቢረዳዳ በአጭር ጊዜ የቫይረሱን ስርጭት ማስቆም ይቻላል ብሏል፡፡

ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል ወይዘሪት ቦንቱ በሪ እንደተናገሩት የከተማ አስተዳደሩ ችግረኛ ወገኖችን ለመርዳት ያደረገው ድጋፍ ተስፋ ሰጪ ነው፡፡

የአስተዳደሩን ጥረት ያህል ነዋሪው ራሱን ከቫይረሱ እንደማይጠበቅ ገልፀው ችግሩ የከፋ ጉዳት ሳያስከትል አስቀድመን መጠንቀቅ አለብን ብለዋል ።

ለአረጋውያን፣ ደጋፊ ለሌላቸውና ከኤች.አይ.ቪ. ኤድስ ጋር የሚኖሩ ወገኖች ከተደረጉ ድጋፎች መካከል ምግብ፣ አልባሳት፣ ዘይት፣ ለኢድ-አልፈጥር በዓል ማክበሪያ የሚሆኑ በጎች ይኙበታል፡፡

ከ20 የሚበልጡ የደወልሽ ይሰማ በጎ አድራጎት ማህበር አባላት ከቁሳቁስ እገዛ በተጨማሪ የደም ልገሳ አካሂደዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም