በሰሜን ጎንደር የአትሌቲክስ መንደሮች ግንባታ እየተካሄደ ነው

75

ጎንደር (ኢዜአ) ግንቦት 15/2012  በሰሜን ጎንደር ዞን በደባርቅና በዳባት ከተሞች ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሁለት አትሌቲክስ መንደሮች ግንባታ እየተካሔደ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የደባርቅ ወረዳ ዋልያ አትሌቲክስ ክለብ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ማንደፍሮ አበበ ለኢዜአ እንደተናገሩት ከደባርቅ ወረዳ አስተዳደር ለአትሌቲክስ መንደሩ ግንባታ የሚውል 3 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ክለቡ ተረክቧል፡፡

በአሁኑ ወቅት የቦታ ማጽዳት ስራ እየተካሔደ መሆኑን ገልፀው ለአትሌቲክስ መንደሩ ግንባታ የሚያስፈልገውን 15 ሚሊዮን ብር የዞኑና የደባርቅ ወረዳ መስተዳድር፤ የክልሉ መንግስት ፣ የደባርቅ ዩኒቨርሲቲና ሌሎች አጋር አካላት ድጋፍ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል ።

የአትሌቲክስ መንደሩ ግንባታ አምስት አመትየሚወስድ ሲሆን እስከ 300 የሚደርሱ አትሌቶችን በመቀበል በዘርፉ በሃገር ውስጥም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ ብቁ ተወዳዳሪዎችን ለማፍራት የሚያግዝ ነው፡፡

ግንባታው የአትሌቶች መኖሪያ፣ የምግብ አደራሽ፣ ጂምናዚየም፣ የመሮጫ መምና የአስተዳደር ቢሮዎችን የሚያካትት ይሆናል ብለዋል።

የአትሌቲክስ መንደሩ የእግር፣ የእጅ፣ የመረብና የቅርጫት ኳስ ስፖርቶች በፕሮጀክት ደረጃ የሚካሄድበት ሲሆን በረጅም ጊዜ እቅድ ደግሞ ወደ ስፖርት አካዳሚ ለመቀየር ውጥን መኖሩን ዋና ስራ አስፈጸሚው አመልክተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ከወረዳው መስተዳድር በተመደበ 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ወጪ 6 ክፍሎች ያሉት ጊዚያዊ የአትሌቶች መኖሪያ ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በተመሳሳይ በዳባት ከተማ 150 አትሌቶችን የማስተናገድ አቅም ያለው ዘመናዊ የአትሌቲክስ መንደር ግንባታ መጀመሩን የዞኑ ማህበራዊ ልማት መምሪያ የስፖርት ቡድን መሪ አቶ አየልኝ ካሳ ተናግረዋል፡፡

ለመጀመሪያው የግንባታ ምእራፍ 4 ሚሊዮን ብር ተመድቦ ወደ ስራ የተገባ ሲሆን የዳባት ከተማ አስተዳደርም 16 ሺህ ካሬ ሜትር የሚጠጋ ቦታ ለግንባታ ስራው በነጻ መስጠቱን ገልፀዋል።

አሁን ላይ 30 በመቶ ግንባታው የተጠናቀቀው አትሌቲክስ መንደሩ 28 ክፍሎች ያሉት ሲሆን የአትሌቶች መኖሪያ፣ የምግብ አዳራሽ፣ ጂምናዚየም የሴቶችና የወንዶች ሻወርና መፀዳጃ ቤቶችን ያካተተ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ለሁለተኛው የግንባታ ምእራፍ በተመደበው 3 ሚሊዮን ብር ደግሞ የመሮጫ መም፣ የእጅ፣ የእግርና የመረብ ኳስ እንዲሁም የሜዳ ቴኒስ የስፖርት ማዘውተሪያ ሰፍራዎች በቀጣዩ አዲስ አመት ግንባታቸው ይጀመራል፡፡

የዳባት አትሌቲክስ መንደር በሃገሪቱ የመጀመሪያው የአትሌቲክስ ኢንስትራክተር የነበሩት የአቶ እንዳልክ ቀለመወርቅ የትውልድ ስፍራ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም