በአማራ ክልል 25 ወረዳዎች የተከሰተውን የወባ ወረርሽኝ እየተከላከልን ነው - የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት

158

ባህር ዳር፣ ግንቦት 15/2012 ዓ.ም  (ኢዜአ) በአማራ ክልል ቆላማ በሆኑ 25 ወረዳዎች የተከሰተውን የወባ ወረርሽኝ የመከላከል ስራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማህተመ ሃይሌ  በትላንትናው ዕለት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳሉት የወባ በሽታው የተከሰተው ከሚያዚያ ወር 2012 ዓ/ም ጀምሮ ነው።

“የክልሉ መልከአ ምድር አቀማመጥ 80 ከመቶው ለወባ መራቢያ ምቹ መሆኑና ህብረተሰቡ ትኩረቱን ኮሮና ቫይረስ ላይ ማድረጉ በሽታው እንዲስፋፋ ሆኗል”ብለዋል።

እስከ አሁንም በክልሉ ውስጥ ባሉ ወረዳዎች በሙሉ በሚባል ደረጃ የወባ በሽታ ምልክት መታየቱን ጠቅሰዋል።

እንደ ዶክተር ማህተመ ገለጻ በሽታው በምዕራብ ጎንደር፣ ማዕከላዊ ጎንደር፣ አዊ ብሄረሰብ አስተዳደር እና ምዕራብ ጎጃም ዞኖች ውስጥ በሚገኙ 25 ወረዳዎች ደግሞ በወረርሽኝ መልክ ተከስቷል።

ወረርሽኙ ከተከሰተባቸው ወረዳዎች መካከል መተማ፣ ቋራ፣ ታች አርማጪሆ፣ ምዕራብ አርማጭሆ፣ ጃዊና ባህር ዳር ዙሪያ ወረዳዎች ይገኙበታል”ብለዋል።

በዚህ አመት በክልሉ ከ400 ሺህ የሚበልጡ ሰዎች በወባ በሽታ መያዛቸውን ጠቅሰው፤ ይህም ከባለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር በ73 በመቶ ብልጫ እንዳለው አመልክተዋል።

“ያቆሩ ኩሬዎችን ማፋሰስና አጎበርን በአግባቡ መጠቀም የወባ በሽታን ለመከላከል አይነተኛ መስፈርቶች ቢሆኑም ህብረተሰቡ ግን ይህንን እያደረገ አይደለም”ብለዋል።

ችግሩን ለመቀነስና ለመከላከልም ህብረተሰቡ ትኩረቱን ከወቅታዊ የኮሮና ቫይረስ ጎን ለጎን የወባ በሽታን ለመከላከልም አንድ ቡድን ተቋቁሞ የግንዛቤ መፍጠር ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

“በተጨማሪም በቆላማ ቦታዎች የሚከሰተውን የወባ በሽታ ለመከላከል 110 የጤና ባለሙያዎችን በማሰልጠን ህክምና እንዲሰጡ የምልመላ ስራ እየተከናወነ ይገኛል”ብለዋል።

በቅርቡም የኬሚካል ርጭት ለማካሄድ 260 ሺህ ኪሎ ግራም ኬሚካል መቅረቡን አመልክተው፤ ችግሩ በከፋባቸው አካባቢዎች ርጭቱ እንደሚከናወን ጠቁመዋል።

መንግስት በሽታውን ለመከላከል ከሚያደርገው ጥረት በተጨማሪም ህብረተሰቡ የወባ ትንኝ መራቢያ የሆኑ ቦታዎችን በመለየት የማጽዳት ስራ መስራት እንዳለበትም አሳስበዋል።

“የወባ በሽታ ገዳይ ከሚባሉት በሽታዎች በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ በመሆኑ ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ ማቅለሽለሽና መሰል የበሽታው ምልክቶች የታየበት ግለሰብ በፍጥነት በአቅራቢያው ወደ ሚገኝ ጤና ተቋም በመሄድ መታከም ይገባዋል”ብለዋል።

በሽታውን ለመከላከል የጤና ተቋማት ጥረት ብቻ ሳይሆን በየደረጃው የሚገኝ አመራር የቁልፍ ተግባራት አንዱ አካል አድርጎ ሊንቀሳቀስ እንደሚገባም ዶክተር ማህተመ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም